Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን መደበኛ ስብሰባ አጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፈ አጠናቀቀ፡፡

ኮሚቴው በሰላም፣ በልማት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና መጪዉን ሃገራዊ ምርጫ በተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በዋናነት ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል በሃገሪቱ የታየው ለውጥ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ፈተናዎችን ተጋፍጦ የሃገሪቱን ብልጽግና እውን ለማድረግ ሰፊ እድል የፈጠረና ሃገሪቱን ከብተና አደጋ ያዳነ መሆኑ በውይይቱ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

በተለይም ብልጽግና ውህድ ህብረ ብሄራዊ ሃገራዊ ፓርቲ ሆኖ መደራጀቱ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ከፍተኛ እድል ከመፍጠሩም በላይ ከሃገሪቱ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ተገለዉ የዳር ተመልካች የነበሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማቀፍና ለማሳተፍ የቻለ የመጭው ትዉልድ ፓርቲ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በስብሰባው በሃገራዊ ለዉጡ የተገኙ ድሎችን ጠብቆ በማስቀጠል ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን ለዚህም የፓርቲውን መርሆዎች፣ እሴቶችና አሰራሮችን በጥብቅ ስነ ምግባር ተግባራዊ ማድረግና ጠንካራ ተቋማዊ ባህል መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

ኮሚቴው በሁለቱ ቀናት መደበኛ ስብሰባዉ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች አስቀምጧል፡፡

ሃገሪቱን ለመበታተን በከፍተኛ ሁኔታ ሲዘጋጅ ቆይቶ ፍጹም አረመኔያዊ በሆነ መልኩ በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል፡፡

ይህ ስግብግብ ጁንታ በአጭር ጊዜ እንዲፈርስና ሃገሪቱ ከዚህ ከሃዲ ሃይል ነጻ እንድትወጣ ጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራና አፋር ክልሎች ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ድጋፍ ላደረጉ መላው የሀገሪቱ ህዝቦች ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ ጀግንነት ልምዳችን ስለሆነ በዚህ ድል ሳንኩራራ ይህንን ሃገራዊ የአንድነት ስሜትና ቁርጠኝነት በሌሎች የልማት ዘርፎችም በመድገም የሃገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ርብርብ እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የወንጀለኛውን ከሃዲ ጁንታ አባላት ከተደበቁበት አድኖ ለፍርድ ለማቅረብ ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን በህግ ማስከበር እርምጃው ሂደት ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና እብሪተኛው ጁንታ ያፈራረሳቸው የህዝብ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በትግራይ ክልል የህዝብ አገልግሎቶችን ለማስጀመር፣ የእለት ደራሽ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ለማድረስና ህብረተሰቡ ወደ መደበኛ የእለት ተእለት ህይወቱ እንዲመለስ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው የሃገሪቱ ህዝቦች የቻሉትን አስተዋጽኦ ሁሉ እንዲያደርጉ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡

በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስትና ብሄረ መንግስት ግንባታ ሂደት የተለያዩ የፖለቲካ ሃይል አሰላለፎች የሚታዩበት ነው፡፡

በሃገሪቱ የሚታየውን ውስብስብ ብዝሃነት የሚያስተናግድ ሃገራዊ አንድነት ከመገንባት አንጻር በወንድማማችነት እሴት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያረጋግጥ የፌደራል ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን የፓርቲው አመራሮችና አባላት በቁርጠኝነት እንዲታገሉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቦች የሚያነሷቸው የማንነት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው ፍትሃዊ የህዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን ኮሚቴው ያምናል፡፡

እነዚህ ጥያቄዎች ነባራዊ ሁኔታውን መሰረት በማድረግ የህዝቦችን ወንድማማችነትና አብሮነት እንዲሁም የህዝቡን ነጻ ፍላጎት ከግምት ባስገባ መልኩ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ ምላሽ እንዲሰጣቸው ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ተገቢው እርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ኮሚቴው ከስምምነት ደርሷል፡፡

እነዚህን እኩይ ተግባራት የሚፈጽሙ የጥፋት ሀይሎች በቁጥጥር ሥር ለማዋልና እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ርብርብ በየደረጃው የሚገኙ የብልጽግና አመራሮች በከፍተኛ ጽናትና ቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የሃገሪቱን ፖቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የብልጽግና አመራሮችና አባላት ከሚለያዩ ጥቃቅን ጉዳዮች ወጥተው ከፍ ያለ ሃገራዊ እይታ በመያዝ ኢትዮጵያንና የሁሉንም ዜጎቿን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን በሚያደርግ መልኩ እንዲደጋገፉ፣ እንዲረዳዱ፣ በአብሮነትና በትብብር መንፈስ መስራት እንደሚገባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በ2013 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ሃገሪቱን ወደ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለምታደርገው ሽግግር ያለው ትርጉም እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል፡፡ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና በሂደቱ ሆነ በውጤቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የብልጽግና አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቅጣጫተቀምጧል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ምርጫ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ በውጤታማነት እንዲያጠናቅቅ በፓርቲው ማኒፌስቶ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ አጽድቆታል፡፡ መላው የፓርቲው አመራሮችና አባላት የጸደቀውን ማኒፌስቶ መሰረት በማድረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በሃገሪቱ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመሸጋገር የተወሰዱ የሃገራዊ ለውጥ እርምጃዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መጭዉ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና በሂደቱም ሆነ በዉጤቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

መላውየሃገሪቱ ህዝቦች ባለፉት ሁለት ተኩል አመታት በኢትዮጵያ የታዩ ለውጦችና የተገኙ ድሎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ መጭውሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅና የዜጎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግና የተረጋገጠባት ጠንካራ ሃገር ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ብልጽግናፓርቲ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.