Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎች ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል የአንድ ወር ደመወዝ 50 በመቶ ለገሱ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎች በትግራይ ክልልና በመተከል ዞን ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ከወር ደመወዛቸው 50 በመቶ ለገሱ

መንግሥት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም፣ ሰብዓዊ እርዳታን ለማዳረስና የህብረተሰቡን የእለት ተእለት ኑሮ ሰላማዊና የተረጋጋ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ በመሆኑ ለውጦች መታየታቸውን የፓርቲው ሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥታትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉ በተላለፈው ጥሪ መሠረት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ የክልል መንግሥታት፣ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በጥሪው መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ የሚውል የአንድ ወር ደመወዛቸውን፣ ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ 200 ሺህ ብር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል ሦስት የውኃ ማመላለሻ ባለታንከር መኪናዎችን መደገፋቸውን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በትግራይ ክልልና በመተከል ዞን ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ እያደረገ ያለው ርብርብ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ኀላፊው የተናገሩት።

መንግሥት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ እንዲደርስ፣ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡና ህብረተሰቡ በዘላቂነት እንዲቋቋም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች መንግሥትና ህብረተሰቡ ለወገኖቹ ለመድረስ እያደረገ ያለውን ርብርብ ለማበረታታት የአንድ ወር ደመወዛቸውን 50 በመቶ መለገሳቸውን የገለጹት ዶክተር ቢቂላ ፤የዜጎች መደበኛ ህይወት እስከሚስተካከል ድረስ በየደረጃው ያለው አመራር የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋናው ጽሕፈት ቤት የሥራ ኀላፊዎች የልማት ሥራዎችን በመደገፍ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑንና ከዚህ በፊት ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የአንድ ወር ደመወዝ እንደለገሱ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.