Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ፡፡

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለአንድ ቀን በሚያካሂደው ስብሰባ ፥ የብልፅግና ፓርቲ 1ኛ ጉባዔ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ከሊጉ አባላት ጋር በየደረጃው የተደረገውን ውይይት አፈፃፀም እንደሚገመግም ተገልጿል፡፡

“ምግቤን ከጓሮዬ፤ ጤናዬን ከምግቤ” በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቱ የተጀመረው የከተማ ግብርና ንቅናቄ የአፈፃፀም ደረጃ በየክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ይደረጋልም ተብሏል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ በቅርቡ የመጀመሪያ ጉባዔውን እንደሚያደርግ እና ለጉባዔው በሚቀርቡ ሰነዶች ላይ መወያየትም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የዛሬ አጀንዳ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ለጉባዔው የሚቀርብ ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን ፥ ስራ አስፈፃሚው የማሻሻያ ሃሳቦችን በማከል ለቅድመ ጉባዔ ውይይቶች እንዲቀርብ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ፥ ሊጉ እስካሁን በሚጠቀምባቸው ፕሮግራም፣ ህገ ደንብ እና የአሰራርና አደረጃጀት መመሪያዎች ላይ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየትም ለሊጉ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያቀርባል መባሉን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ስራ አስፈጻሚው በውይይቱ የሚደርስባቸው የግምገማ ውጤቶችና መነሻ ሃሳቦች በነገው እለት ለሚካሄደው የሊጉ የማዕካላዊ ኮሚቴ ውይይት ቀርበው አቅጣጫ ይቀመጥባቸዋልም ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.