Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ለሽሬ እና አካባቢው ነዋሪዎች አልሚ ምግብና መድሃኒት ላከ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ለሽሬ እና አካባቢው ነዋሪዎች 500 ኩንታል አልሚ ምግብና መድሃኒት ድጋፍ ወደ ስፍራው መላኩ ተገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ አልሚ ምግቦቹ እና መድሃኒቶቹ በፍጥነት ወደ ስፍራው እንዲደርሱ በማሰብ በኢፌዴሪ አየር ሃይል እቃ ጫኝ አውሮፕላን አጓጉዟል፡፡

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ፤ ቁሳቁሱ ወደ ስፍራው በተላከበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ችግር ለገጠማቸው ዜጎች ድጋፍ የማድረስ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል መቀሌን ማዕከል በማድረግ ለሁሉም አካባቢዎች እርዳታ ማድረሱንም አስታውሰዋል።

በዛሬው ዕለትም ለህጻናት እና እናቶች የሚውል 500 ኩንታል አልሚ ምግብ ለሸሬ እና አከባቢዋ ነዋሪዎች መላኩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ2 ሚልየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ መድሃኒቶች ወደ ስፍራው መላኩንም ኮሚሽነር ምትኩ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል እስካሁን በኮሚሽኑ በኩል ለ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍና እርዳታ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

እርዳታው በተለይ ከተሞች አካባቢ በህግ ማስከበር ሂደቱ ገቢያቸው ለተቋረጠባቸው ወገኞች እና በገጠርም አካባቢ ላሉት ነዋሪዎች መድረሱን ያመላከቱ ሲሆን፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በሀገሪቱ ሌሎች እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚውል 20 ሺህ ሜትሪክ ቆን እህል ከውጭ እየገባ መሆኑንም ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.