Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ አካላት በአፋር ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲውዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና በሶማሊያ የተሰማራው አሚሶም የሰላም አስከባሪ በአፋር ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ፡፡

በሲውዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአፋር ክልል በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የ1 ሚሊየን 147 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ዘመቻ ለህልውና በሚል በሲውዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያን ያሰባሰቡትን ገንዘብ በተወካዮቻቸው አማካይነት ዛሬ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛሃራ ሁመድ አስረክበዋል፡፡

የዳያስፖራ አባላት በአፋር ክልል የደረሰውን ውድመት እና ኢ- ሰብአዊ ድርጊት በስፍራው ተገኝተው መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በአፋር ክልል የተመለከቱት ነገር እንዳሳዘናቸው ገልጸው ፥ የደረሰው ውድመት እና የሞራል ስብራት መጠገን የሚቻለው ማህበረሰቡ አስቀድሞ ከነበረው የተሻለ ነገር ማድረግ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ የወደሙ ተቋማትን ለመገንባት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በሶማሊያ የተሰማራው አሚሶም የሰላም አስከባሪ ለአፋር ክልል ከ752 ሺህ ብር በላይ ገንዘብና የአይነት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን ያስረከቡት በሶማሊያ አሚሶም የአራተኛ ሴክተር የሰላም አስከባሪ አዛዥ ኮሎኔል የሸዋስ ቀረበት ፥ ሰራዊቱ ከሚያገኘው ላይ ቀንሶ ለህዝቡ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ህዝቡ ወደ ቀደመው ህይወቱ እስኪመለስ ድረስ ድጋፋቸውን እንደማያቋርጡም ተናግረዋል።

ድጋፋን የተረከቡት የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሃራ ሁመድ ለተደረገውን ድጋፍ አመስግነው ፥ በአፋር ክልል የደረሰው ችግር የኔም ነው በማለት ህዝቡ አለኝታነቱን ያሳየበት ነው ብለዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ ወደ ነበረችበት ልማት ለመመለስ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::

በቅድስት ብርሃኑ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.