Fana: At a Speed of Life!

የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በተመለከተ የሰጡት መግለጫ አግባብነት የሌለውና አድሏዊ ነው – በጄኔቫ የኢትዮጵያውያን የድርጊት ግብረ ሃይል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀመጫቸውን በአውሮፓ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ተቋማት በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰጡት መግለጫ አግባብነት የሌለውና የኮሚሽኑን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል መሆኑን አስታወቁ፡፡

በጄኔቫ የኢትዮጵያውያን የድርጊት ግብረ ሃይል የተዘጋጀውና መቀመጫቸውን አውሮፓ ያደረጉ የኢትዮጵያውያን የተለያዩ ማህበራትና ተቋማት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፅህፈት ቤት፥ መንግስት በትግራይ ክልል ከወሰደው ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ በሰጠው መግለጫ ላይ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

በደብዳቤያቸውም የተመድ ሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚቼል ባችሌት በትግራይ ክልል ከተወሰደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ በፈረንጆቹ ታህሳስ 22 ቀን የሰጡት መግለጫና አስተያያት እጅጉን እንዳስከፋቸው ገልጸዋል፡፡

ፅህፈት ቤቱ ለንጹሃን ሰብአዊ መብት የሰጠውን ትኩረት ያወደሱት ተቋማቱ፥ ይሁን እንጅ ኮሚሽነሯ ያለምን ተጨባጭ ማስረጃና ከግል ፍላጎት በመነጨ መልኩ ያቀረቡት ውንጅላና አድሏዊ አካሄድ የኮሚሽኑ ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነውም ብለዋል፡፡

አያይዘውም ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን ለቀረቡለት የሰብአዊ መብት ጥሰት አቤቱታ የሰጠው የዝምታ ምላሽ በቀላሉ የሚረሳ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡

በበርካታ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተሰንዶ ለኮሚሽኑ የቀረበውና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈጸመበት የህወሓት ጨቋኝ የአገዛዝ ዘመንን የሚያሳየው ሪፖርት በኮሚሽነሯ መግለጫ ሆን ተብሎ እንዲተው የተደረገበት መንገድም እጅግ አሳዛኝ ነውም ብለዋል በደብዳቤያቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም መግለጫው ባለፈው ህዳር ወር በህወሓት አማካኝነት በማይካድራ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ እና ህወሓት የህግ ማስከበር ዘመቻውን ዓለም አቀፋዊ ቅርጽ ለመስጠት ወደ ኤርትራ ያስወነጨፋቸውን ሮኬቶች እና በርካታ ህዝብ በሚኖርባቸው የጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች ያደረገውን የጥቃት ሙከራ ያላካተተ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የፅህፈት ቤቱን ገለልተኛና ነጻ ያልሆነ አካሄድ በተቹበት ደብዳቤ መግለጫው ህውሓት በተለያዩ የመሰረተ ልማት ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመትና ጥፋት የካደና መንግስት ለንጹሃን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስና ለመልሶ ግንባታ ለሰጠው ትኩረት እውቅና ያልሰጠ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም ለኮሚሽኑ የደረሰው ሪፖርት መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበና ያልተረጋገጠ አልያም ጊዜ ያለፈበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽነሯ መግለጫው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ ሁመራን በመቆጣጠር በንጹሃን ላይ ግድያ በመፈጸም ሆስፒታልና ባንኮችን ጨምሮ ዝርፊያ ፈጽመዋል በሚል በህወሓት የተፈበረከውን ውንጀላ ያስተጋባ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም መግለጫው መከላከያ ሰራዊትን እና የአማራ “ፋኖ”ን ስም ያጠለሸ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ያነሳው ደብዳቤው፥ ፅህፈት ቤቱም ተቋማዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣና ራሱን ከሃሰተኛ መረጃ እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.