Fana: At a Speed of Life!

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በጠራው ስብሰባ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ኢትዮጵያ እንደማትቀበል አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በመጪው ዓርብ እንዲካሄድ የጠራውን ልዩ ስብሰባ እንደማይቀበልና በዚህ ስብሰባ የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ።

ከትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ጋር በተያያዘ በመጪው ዓርብ እንዲካሄድ የተጠራው ልዩ ስብሰባ የሚካሄድበትን ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ የምክር ቤቱ ቢሮ ትናንት በተወያየበት ወቅት በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ አምባሳደር ማሕሌት ኃይሉ ተገኝተው የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም በግልጽ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የተጠራው ልዩ ስብሰባ የምክር ቤቱን የአሠራር ደንብ ያልተከተለና የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ ለፖለቲካዊ ፍላጎቶች መጠቀሚያ የሚያደርግ እንዲሁም፥ ምክር ቤቱ አባል አገራት ላይ መድሎ እንዲፈጽምና በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያዩ አሠራሮችን እንዲከተል በማድረግ ተቋማዊ ኃላፊነቱን የሚያረክስ መሆኑን ተናግረዋል።

አባል አገራቱ ይህንን ያልተገባ አሠራርና አንዳንድ አገራት ሰብዓዊ መብትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በምክር ቤቱ በኩል ለማስፈጸም የሚያደርጉትን ጥረት በማውገዝ የምክር ቤቱ ተቋማዊ መርሆዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

“የተጠራው ልዩ ስብሰባና ምክር ቤቱ በዚህ ስብሰባ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተብሎ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ጋር በቀጥታ የሚጣረስ በመሆኑ ስብሰባውም ሆነ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ እንዲሰረዙ እንጠይቃለን” ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶችን የሚመረምር ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ እንዲሰማራ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በአውሮፓ ኅብረት አማካይነት ለምክር ቤቱ መቅረቡን ሪፖርተር ዘግቧል።

ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር በጥምረት ያደረጉት ምርመራ ውጤትን መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲሰማራ የሚጠይቅ ነው።

ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድኑ የአንድ ዓመት ቆይታ እንዲኖረው የሚጠይቀው ይህ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ የሚላከው ቡድን ከሚያደርገው ምርመራ በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ የሚደረግበትን፣ ዕርቅና ተጠያቂነት የሚሰፍንበትን እንዲሁም፣ ሰብዓዊ ጥሰት የደረሰባቸው ማገገም እንዲችሉ ምክረ ሐሳብና የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት እንዲኖረውም ይጠይቃል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.