Fana: At a Speed of Life!

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚገነዘብ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በጄኔቭ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዋና ኃላፊ ፍራንሱዋስ ሚያንዳ መንግስት በትግራይ ክልል ስለወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ሰፊ ገለፃ ሰጥተዋል።

የሕወሓት ጁንታ ቡድን የተደራጀ ምዝበራ እና በወታደራዊ ኃይል የታገዝ መጠነ ሰፊ የሕግ ጥሰት ሲፈፅም መቆየቱንና የኢትዮጵያን ሕልውና ጭምር አደጋ ላይ ለመጣል ሌት ተቀን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀውላቸዋል።

በሃገሪቱ እየተተገበረ ባለው መሠረታዊ የሪፎርም ሥራ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ መሻሻሎች እየተመዘገቡ ቢሆንም፣ ቡድኑ የለውጡ አካል ሆኖ በሠላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ ይልቅ፣ ለውጡን ቀልብሶ ወደ ስልጣን በመመለስ የፖለቲካ ተጽዕኖውን እና የኢኮኖሚ ምዝበራውን ለማስቀጠል ሃገርን የማተራመስና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ላይ ተሰማርቶ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ያሳየውን ሆደ ሰፊነት እንደ ድክመት እና ፍርሀት በመውሰድ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ አባላትን በማጥቃት እና ከባድ መሳሪያዎችን በመዝረፍ ፈጽሞ ከስህተቱ የማይማር ድርጅት መሆኑን ማሳየቱን አንስተዋል።

ይህን ተከትሎም መንግስት ሕግ የማስከበር ዘመቻውን መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሕግ የማስከበር ዘመቻው መጠናቀቁን፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን እና ሕብረተሰቡ ወደ ዕለት ተዕለት ኑሮው እየተመለሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ በኋላ የሚቀረው የጁንታው ቡድን አባላትን አድኖ ወደ ሕግ ፊት የማቅረብ ስራ መሆኑን እና ይህም በፌደራል ፖሊስ በኩል እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የስልክ፣ የመብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ገለፃ አድርገዋል።

አያይዘውም መንግስት ከዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት ጋር ተባብሮ እየሠራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው፣ ወደ ጎረቤት ሃገር የተሰደዱ ዜጎችንም ወደ ሃገራቸው ተመልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታ ከሚመለከታቸው የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ፣ ለዚሁም አራት የመጠለያ ካምፖች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ለማጥናት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የጥናት ቡድኖችን ልኮ ካጣራ በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተላለፊያ መስመር በመክፈት አስፈላጊውን ድጋፍ በማከፋፈል ላይ መሆኑን፣ በሠላም ሚኒስቴር አስተባባሪነትም ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ለማቅረብ እንዲቻል እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስረድተዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዋና ኃላፊ ፍራንሱዋስ ሚያንዳ በበኩላቸው ኮሚሽነር ጽህፈት ቤቱ እንደሰብዓዊ መብቶች ተቋም የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ፣ ተፈናቃዮች ተገቢው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻች ያበረታታል ብለዋል፡፡

እንዲሁም በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት አለመኖሩን፣ መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎችን ጽህፈት ቤቱ በቅርበት የሚከታተልና የሚደግፍ መሆኑንመግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.