Fana: At a Speed of Life!

የተግባር ሰው በመሆን፣ በጀግንነት በመቆምና መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን እናጸናለን – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የኦሮሞ ህዝብ ትናንት እንደ ህዝብ የተወጋውን ውግ፣ የወጋውን ጠላትም ሆነ የተወጋበትን ጦር ይረሳ ዘንድ በፍጹም አይችልም፡፡ የተፈጸመብንን ግፍ፣ የተጎነጨነውን መራራ የመከራ ጽዋ፣ ተጭነው የገፉንን የግፍ እጆች፣ አንገታችንን ቆልምመው በሀፍረት ያስጎነበሱንን የወራሪው እና የአሸባሪውን ትህነግ የባርነት መዳፎች፣ ከሰውነት ተርታ አውርደው ትቢያ ላይ የረገጡንን ጨካኝ እግሮቹን መቼም አንረሳቸውም፡፡
ገዳዮቻችን መግደላቸውን ቢዘነጉ ወይም ቢያዘናጉ እንኳ እኛ ግን ሞት እና እንባው- ዋይታው – ሰቀቀን እና እሪታው- ሀዘን እና መጎሳቆሉ መናቅ እና መበደሉ ከልባችን አለና አንዘነጋውም፡፡
ረስተን ሳይሆን ትተን፣ ለበቀል ሳይሆን ለይቅርታ ጀግነን ህዝብ እና አገርን ብለን የተውነው ጠላታችን ለሌላ ሞት፣ ለሌላ እንግልት፣ ለሌላ ስደት፣ ለሌላ ባርነት ሊያጨን ደም እና እውነት አላስቀምጥ ብለውት ከህጻን እስከ ሽማግሌ በማዝመት ለሁለተኛ ዙር ባርነት ቀንበር ሊጭንብን መደንፋት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡
በመሆኑም ውጭ ካሉ ጌቶቹ እና እኛው ውስጥ ከተሰገሰጉ አሽከሮቹ ጋር አገር የማፍረስ ሰፊ ሴራ አሲረው በሰው ልጆች – ያውም በገዛ ወገን ላይ ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እና እልቂት በንጹሀን ላይ እያደረሱ ለዳግም መከራ ሊያጩን መፍጨርጨራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ይህንኑ አደገኛ አካሄዳቸውን ተከትሎም ሰው በላውን ጁንታም ሆነ አሽከሩ ሸኔን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት እና ከኢትዮጵያ ህዝብ ትከሻ ላይ ለአንድ እና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅሎ ግብአተ መሬቱን ለማጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ራሳቸው ግንባር በመዝመት ጦሩን ለመምራት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የታላቋን ኢትዮጵያ ታላቅ ድል ለመላ ኢትዮጵያውያን ለማብሰር የወሰኑትን ቆራጥ ውሳኔ እና ያስተላለፉትን ታሪካዊ አገራዊ ጥሪ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና መላው የኦሮሞ ህዝብ በፍጹም አድናቆት፣ ፍቅር፣ ክብር እና ተነሳሽነት ተቀብለውታል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አመራሮችም የመሪያችንን ወቅታዊ እና አገራዊ ጥሪ በፍጹም ልበ ሙሉነት ተቀብለን፤ እኛም እንደ አባቶቻችን ሁሉ በክብር በደም እና በአጥንታችን መስዋዕትነት ከፍለን የተከበረች አገር ለልጆቻችን ለማቆየት እንዲሁም በልማት እና በአስተዳደር ስራ መስክም የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አገራችንን ከተጋረጠባት ፈተና ለመታደግ ዝግጁ መሆናችንን በቆራጥነት እናረጋግጣለን፡፡
የክልላችን ህዝብም የልጁን- የመሪውን እና አገር እና ህዝቡን ለመታደግ ጦር ሜዳ የወረደውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብሎ ሁሉም ከያለበት ነቅሎ በመውጣት የጠላቶቻችንን፤ የሸኔን እና የአሸባሪው የትህነግን ቀብር በመፈጸም አገራዊ ነቀርሳነታቸው ለአንድ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም እንዲያደርግ ጥሪዬን በአክብሮት አስተላልፋለሁ፡፡
ትናንት ባዶ እጃቸውን ታንክ፣ መድፍ እና መትረየስ ፊት ቆመው ወያኔን ወደወጣበት ዋሻ የመለሱት ቄሮ እና ቀሬዎቻችን ዛሬም እንደገና ላስገብራቹ- እንደገና ልግዛቹ- እንደገና ልዝረፋቹ ብሎ የመጣውን ይህንን እብሪተኛ ሀይል ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጥሪ ተቀብለው ነቅለው በመውጣት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንን በመቀላቀል እና በጦር ሜዳ ጀብዱ የእነ አብዲሳ አጋ፣ ባልቻ ሳፎ፣ ገረሱ ዱኪ፣ የጃጋማ ኬሎ ልጆች እንደሆኑ ዳግም እንዲያስመሰክሩ ታሪካዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ የመመከቱ ታሪካዊ ሀላፊነት እንዳለ ሆኖ በገባንበት ጦርነት ሳቢያ አገራችን ወደማንቆጣጠረው የከፋ የኢኮኖሚ ችግር እንዳትገባ ደጀን ህዝባችን ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በልማት ስራና በየተሰማራበት መስክ ሁሉ ውጤታማ ስራዎችን በመስራት፣ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ የዚህ ታሪካዊ ምእራፍ አሻራ ባለቤት እንዲሆን አደራ እላለሁ፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ህዝብ በየእምነቱ እና አምልኮቱ ጥላ ስር ሆኖ በዱኣ እና በጸሎት ሀገሩን እንዲያግዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ!
ምንም ጥርጥር የለውም እግዚአብሄር ይረዳናል፡፡ ኢትዮጵያ እንደለመደችው በአጭር ጊዜ አሸንፋ በጠላቶቿ መቃብር ላይ ክቡር ሰንደቋን ትሰቅላለች፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.