Fana: At a Speed of Life!

የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትብብር እየተሰራ ነው – አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በተለያየ ጊዜ ከክልሉና ከሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትብብር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ በወቅት እንደገለፁት፥ ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከተለያዩ የክልል ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ቀያቸው ለመመለስ በክልሎቹ በአመራር ደረጃ እስከ ወረዳ የዘለቀ ውይይት መደረጉን አመላክተዋል።

ተፈናቃዮችን ያለምንም ስጋት መመለስ እንዲቻል የፀጥታ መዋቅሩ ሰላም የማስከበር ስራውን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ሰላም መስፈኑ በተረጋገጠባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መመለስ መጀመሩንም አቶ አገኘሁ አስታውቀው፥ ቀሪዎቹን በአስቸኳይ ወደ ቀደመ ቀያቸው በመመለስ የመኸር ወቅት ሳያልፋቸው የግብርና ስራቸውን አንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ ቀያቸው ተመልሰው ለመኖር የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በባለቤትነት እንዲንቀሳቀስም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

“ተፈናቃዮች ሁኔታዎች ተመቻችተው ወደ ቀደመ ቀያቸው እስከሚመለሱ ድረስ መንግስት የእለት ምግብና መሰል ቁሳቁሶችን ከህዝብ ጋር በመተባበር ያቀርባል” ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መካላከል ምግብ ዋስትና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሳይ ማሩ በበኩላቸው፥ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዞኑ የሚኖሩ ዜጎችን ቁጥር ከ21 ሺህ በላይ ደርሷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.