Fana: At a Speed of Life!

የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ የሚያጣራ ሶስት የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ የሚያጣራ ሶስት የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው እና የሳይንስ እና ከፍትኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለያየ አጋጣሚ መንገድ ላይ መታገታቸው ተነስቷል።

በወቅቱ 17 ተማሪዎች ታግተዋል መባሉን ተከትሎ በተደረገ ማጣራትም 12ቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ መሆናቸው መረጋገጡን እና አምስቱ ማንነታቸው እንዳማይታወቅ ተገልጿል።

ከተማሪዎቹ ጋር በተያያዘም መንግስት የደረሰውን መረጃ መሰረት በማድረግ ክትትል እያደረገ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ አሁን ላይም የተማሪዎችን ጉዳይ የሚያጣራ ሶስት የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአካባቢው በትጥቅ የሚንቀሳቀስ አካል መኖሩን እና በተካሄደ ዘመቻ ዋና ዋና ቦታዎችን በመቆጣጠር ቡድኑን መደምሰስ መቻሉን አውስተዋል፤ የቀረው ሃይል ተደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመጥቀስም መንግስት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።

አጠቃላይ እየተደረገ ያለው የምርመራ ሂደት ሲጠናቀቅ ተጨባጭ መረጃ ለህዝቡ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመው፥ ህግ የማስከበር ስራው የፀጥታ አካላት ብቻ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ተማሪዎች ያሉበትን ቦታ በተመለከተ መረጃ መኖሩን እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ ጉዳት ደርሶባቸዋል ከተባለው ጋር በተያያዘ ግን ፖሊስ የደረሰበት መረጃ እንደሌለ አመላክተዋል።

አሁን ላይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተቋማቱ፥ በመንግስት የፀጥታ መዋቅር የቅርብ ክትትል ውስጥ እንዲሆኑ መደረጉም በመግለጫው ተጠቅሷል።

በመግለጫው የተማሪዎቹ እገታ የብሄር መልክ አለው ወይ በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ የስራ ሃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽ፥ በአካባቢው ከዚህ በፊት እገታዎች በዚሁ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ ባለሃብቶች እና አመራሮች ላይ ሲፈጸም መቆየቱን አስታውሰዋል።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ የአንድ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች መያዛቸውን በማንሳት ለእገታው የብሄር መልክ መስጠቱ መሰረት የለውም ብለዋል በምላሻቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው፥ መንግስት ከታገቱ ተማሪዎች ጋር በተያያዘ በሃላፊነት እና በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ንጉሱ ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መንገድ የጀመሩ ተማሪዎች አንፊሎ ወረዳ ሱዲ በተባለ አካባቢ መታገታቸውን አስታውቀዋል።

ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር በተያያዘም የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስፍራው ሁለት ጊዜ በማቅናት መረጃ መሰብሰቡንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በሰላም ሚኒስቴር የተመራ ልዑክ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከሃገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመሆን ከአካባቢው እና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ተወያይቶ ሪፖርት መቅረቡንም አንስተዋል።

መንግስት ከደረሱት የቴክኒክ እና የምርመራ መረጃዎች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ መረጃዎች አግኝቷልም ነው ያሉት፤ መረጃዎቹም እየተደረገ ያለውን የምርመራ ሂደት በማያስተጓጉል መልኩ በየጊዜው ለህዝብ ይፋ እንደሚሆኑ በመጥቀስ።

አያይዘውም በተማሪዎቹ ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሷል በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሃሰት መሆኑን ጠቅሰው፥ መረጃው በህዝብና መንግስት መካከል ክፍተት ለመፍጠር ታስቦ የተሰራጨ ነው ብለዋል በመግለጫቸው።

በተካሄደ ዘመቻም መከላከያ ሰራዊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ የታገቱ 21 ግሰለቦችን ማስለቀቁን ነው የተናገሩት።

የተሳሳተ መረጃ ከመስጠትም የተደረሰበትን ትክክለኛ ውጤትና መረጃ መስጠት በማስፈለጉ በተቀናጀ መልኩ መረጃ መስጠት እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.