Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት መሠረተ ልማት ማነስ ተማሪዎችን ባሉበት ለማስተማር እንቅፋት ሆኗል- ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 3 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትምህርት መሠረተ ልማት አነስተኛ መሆን በኮሮናቫይረስ የተቋረጠውን ትምህርት ለማካካስ በሚደረገው ጥረት ላይ ችግር መፍጠሩን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ሳይቀንስ በ2013 ትምህርት የሚቀጥል ከሆነ የተማሪዎችን ጥግግት ለመቀነስ የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትን ጭምር ለማስተማሪያነት ለመጠቀም መታሰቡንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የኮቪድ-19 ስርጭት በትምህርት ቤቶች እንዳይስፋፋና የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ችግር እንዳይፈጠር መንግስት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህም 26 ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው በቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉን በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መሠረተ ልማት መስፋፋት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ  ገልጸዋል።

የተቋረጠውን የክፍል ውስጥ የገጽ ለገጽ ትምህርት ለማካካስ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ተማሪዎች ባሉበት ሆነው እንዲከታተሉ የማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውንም አስረድተዋል።

ለዚህም እንደ ትምህርት በሬዲዮ፣ የቴሌቪዝን ትምህርት፣ በማህበራዊ ድረ-ገጽ፣ ኦንላይንና መሰል የትምህርት መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም ትምህርት እንዲሰጥ መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል።

ይሁንና እነዚህ የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት በኩል እንደአገር ክፍተት መኖሩንና በታዳጊ ክልሎች ችግሩ የበለጠ የሰፋ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ተደግፎ በሚሰጠው ትምህርት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን  ጠቁመው÷ በመንግስት በኩል ክፍተቱን ለማጥበብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ጫና ለመቀነስ በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በመጠቀም ትምህርት መስጠት ተጀምሮ  እንደነበር ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ይሁንና በአገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ ተማሪዎች የትምህርት መሠረተ ልማትና ቴክኖሎጂ ባልተሟሉባቸው አካባቢዎች መኖራቸው በማካካሻ የትምህርት አሰጣጡ ላይ ይበልጥ ተግዳሮት ማሳደሩን ገልጸዋል።

በቀጣይም የትምህርት ዘርፉን ሊፈታተኑ የሚችሉ ተመሳሳይ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማቶች ክፍተት መሙላት የሚያስችል የ10 ዓመት የትምህርት ልማት ዕቅድ ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

ሚኒስትርዴኤታውአያይዘውም በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ከተከፈቱ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቋቋም ቀደም ሲል ትምህርት ቤቶቻቸውን ከከፈቱ አገራት ልምድና ተሞክሮ እየተወሰደ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.