Fana: At a Speed of Life!

የትዊተር ኩባንያ በ44 ቢሊዮን ዶላር ተሸጠ

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 18፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ አፍሪካዊው ባለሃብት ኢሎን መስክ የትዊትር ኩባንያን በ44 ቢሊዮን ዶላር በመግዛት የግላቸው አደረጉ፡፡

ለወራት ሂደት ላይ የነበረው የትዊተር ኩባንያ የግዥ ሂደት በባለአክሲዮኖችቹ የዳይሬክተሮች ቦርድ እንደተገለጸው፥ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለፀጋው ኢሎን መስክ ያቀረቡት 44 ቢሊዮን ዶላር ተቀባይነትን አግኝቶ ባለሃብቱ ተዊተርን የግላቸው ማድረግ ችለዋል፡፡

ኢሎን መስክ ግዥውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ በነፃነት ሃሳብን መግለፅ የዲሞክራሲ መሰረት ነው ካሉ በኋላ፥ ትዊተርን ደግሞ ለሰው ልጅ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች ላይ ወሳኝ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት የዲጂታል ከተማ አደባባይ ነው ብለውታል።

በአዳዲስ መተግበሪያዎች በማሻሻል የበለጠ ታማኒነት እንዲኖረው በማድረግ ተዊተርን ከምንጊዜውም በላይ ለማዘምን አስራለሁም ሲሉም ባለሃብቱ ተናግረዋል፡፡

ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ ባለፈው ሚያዝያ 4 የኩባንያውን 9 ነጥብ 2% ድርሻ የገዙ ሲሆን፥ በወቅቱ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 40 ዶላር ቢሆንም ኤለን ማስክ ግን በጨረታው የአንድ አክሲዮንን ዋጋ በ54 ነጥብ 20 ዶላር አቅርበዋል፡፡

ኢሎን መስክ የግዥ ዕቅዶቹን ይፋ ካደረገ በኋለ የትዊተር አክሲዮኖች ከ35% በላይ በመጨመር የአንድ አክሲዮን ዋጋ ወደ 52 ዶላር ክፍ ማለቱን የአር ቲ ዘገባ ይጠቁማል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ራሳቸው ኢሎን መስክ በትዊተር ገፃቸው ላይ ያሰፈሩት አንድ መልዕክት በትዊተር ኩባንያ እንዲወርድ ሲደረግባቸው፥ ሀሳቤን የመግለጽ መብቴን ልታፍኑ አትችሉም ሲሉ ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተው እንደነበር ይተወሳል።

አሁን ተዊተርን ጠቅልለው በእጃቸው ያስገቡት የዓለማችን ቁጥር አንድ በለፀጋ፥ ትዊተርን “የሀሳብ ነፃነት መንሸራሸሪያ መድርክ አረድገዋለሁ “ ሲሉ ቃል ገብተዋል።

የሌሎች በርካታ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ፈጣሪ፥ ባለቤትና ባለድርሻ የሆኑት ኢሎን መስክ፥ የተዋቂዎቹ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች አምራች የሆነው የቴስላ ኩባንያ እና በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ቴክኖሎጅ ኮርፖሬሽን የሆነው ሰፔስ ኤከስ ኩባንያ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚም ናቸው።

ደቡብ አፍሪካ ተወላጅ የሆኑት የ51 ዓመቱ ኢሎን መስክ፥ በያዝነው ወር ላይ 273 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሀብት በማስመዝገብ በቢሊየነሮቹ ደረጃ አውጪ ፎርብስ መጽሄት የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት መባል ችለዋል፡፡

በተለይም በህዋ አካላት ኢንዱስትሪ ላይ ስር ነቀል የሆነ አብዮት በማካሄድ የሰው ልጅ የህዋ (የስፔስ) ላይ በረራን በቀላል ወጪ ሊጠቀምበት የሚችልበትን ተስፋ ዕውን ለማድረግ በማለም ከ20 ዓመታት በፊት ስፔስ ኤክስን ( SpaceX) የፈጠሩ ምጡቅ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ጎልማሳ ባለሃብት ናቸው ኢሎን መስክ።

ከካናዳዊት እናትና ከደቡብ አፍሪካዊ አባት የተወለዱት እኝህ ባለፀጋ፥ ደቡብ አፍሪካዊ፥ አሜሪካዊና ካናዳዊ ዜግነት አላቸው።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.