Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ህዝብ በአንድ አጥፊና ካሃዲ ቡድን መገለፅና መወከል እንደማይፈልግ በተግባር አስመስክሯል- የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ህዝብ በአንድ አጥፊና ካሃዲ ቡድን መገለፅና መወከል እንደማይፈልግ በተግባር አስመስክሯል ሲል የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት  ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ይቀርባል።

ሶስተኛውና የመጨረሻው ዙር ህግ የማስከበር ተልእኳችን የህዝብ ህልዉናና ንብረት ለማዳን የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ባሳካ መልኩ በድል በመጠናቀቁና የአጥፊው ቡዱን የመጨረሻ ምሽግ የነበረችው ሰሜናዊት ኮኮብዋ መቐለ ከተማ ነፃ በመውጣትዋ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል፡፡

በትላንትናው ቀን ከወደ ሰሜን የአገራችን ክፍል የተሰማው ይህ የድል ብስራት በጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊታችን አንፀባራቂ ገድል እንዲሁም በመላ ህዝባችን አስደናቂ ርብርብ የተገኘ መሆኑ ድርብ ድል ያደርገዋል፡፡

የትግራይ ህዝብም በከፋ አፈናና ጦርነት ውስጥም ሆኖ የነፃነት ቀኑ ሲጠባበቅና ከመንግስት ይደርሰው የነበረው መልእክትና መመርያ በአግባቡ በመተግበር አጥፊው ጁንታ ቀድሞ ከልቡ አውጥቶት እንደቆየው ሁሉ አሁን ደግሞ ከጉያው ገፍትሮ በመጣል የትግራይ ህዝብ በአንድ አጥፊና ካሃዲ ቡድን መገለፅና መወከል እንደማይፈልግ በተግባር አስመስክሯል፡፡

በቀጣይ የመጨረሻ ሰዓታትም እነዚህ የአለም-አቀፍ የጦርነት ህግጋትም ጭምር በመጣስ ከማንምና ከምንም በላይ አብልጠው የሚወዱት ስግብግብ ነብሳቸው ለማዳን ሲሉ በህዝብ፣ በከተሞችና በእምነት ተቋማት ጉያ ሳይቀር መሽገው የቆዩት የአጥፊ ቡድኑ አባላት አንድ-በአንድ ተለቅመው ለፍርድ የሚቀርቡበት የመጨረሻ ስራ በአጭር ግዜ የሚጠናቀቅ ሲሆን የትግራይ ህዝብ አሁንም እንደተለመደው በዚህ የመጨረሻ ተልእኮ ላይ ቀና ትብብሩ እንዲያሳይ አደራ እንላለን፡፡

የስግብግብ ጁንታው ፍፃሜ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ የትንሳኤና የአዲስ ዘመን ብስራት ነው፡፡

በመሆኑም ይህ በህዝቦች የተባባረ ጥረት የተገኘው አዲስ ዘመን የማስቀጠልና የማስፋት ሃላፊነት አሁንም በየአንዳንዱ ዜጋ ትከሻ ላይ የሚቀመጥ መሆኑ ተገንዝበን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዚህ አጥፊ ቡዱን መሰል ቅሪት አስተሳሰቦችና ተግባራት በቀጣይነት የማፅዳት ስራ አጠናክሮ መቀጠሉ ወሳኝነት እንዳለው መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

ቀጣዩ ግዜም ተንሰራፍቶ የቆየው የክህደት፣ የበደል፣ የሌብነትና የድህነት ምዕራፍ ተዘግቶ የሃቀኝነት፣ የህዝብ አገልጋይነት፣ የፍትህና የብልጽግና አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት ወርቃማና የከፍታ ግዜ ይሆናል፡፡ ይህ እዉን ለማድረግም የኢትዮጵያ ህዝቦች ልክ በፀረ-ጁንታው ትግል ላይ ያሳዩት የአንድነት፣ የመተሳሰብና የመተባበር መንፈስና ወኔ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ምንም ጥርጥር የለዉም፡፡

በአሁኑ ግዜ ይህ የትግራይ ህዝብም የመላ የኢትዮጵያ ህዝብም እዳ ሆኖ የቆየው ዘራፊና ገዳይ ቡዱን እራሱ በቆሰቆሶው እሳት ተለብልቦ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ግብአተ-መሬቱ በመፈፀሙ ሁሉም ዜጋ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ወደ ቀደመው መረጋጋቱና መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ እንዲሁም በአገራዊና በክልላዊ ለውጡ ያለው ንቁ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

ደማቅ ድል ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊታችን፤

ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ነፃነት ለህዝባችን፤

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና መስዋእት

ለዘላለም ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ትኖራለች!!

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት

 

ሕዳር 20፣ 2013 ዓ/ም

 

አዲስ አበባ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.