Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ቴሌቪዥን ያሰራጨው ዘገባ ፍጹም ሀሰት ነው -ቢቢሲ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  የትግራይ ቴሌቪዥን ቢቢሲ “የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የምያንማሯ መሪ አንግ ሳን ሱ ኪ የገጠማቸው አይነት ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ይኖራቸዋል ሲል ቢቢሲ ዘገበ” በማለት ያቀረበው ዜና ፍጹም ውሸት መሆኑን ቢቢሲ አስታውቋል።

የቀድሞው የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍንም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጣቸው የኖቬል የሰላም ሽልማት አይገባቸውም” ሲሉ ለትግራይ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የ2019 የኖቬል የሠላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።

ሆኖም የትግራይ ቴሌቪዥን ሽልማቱ አይገባቸውም በሚል ያሰራጨው ዘገባ ፍጹም ሀሰትና እኛን የማይወክል ነው ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።

“የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የምያንማሯ መሪ አንግ ሳን ሱ ኪ የገጠማቸው አይነት ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ይኖራቸዋል” ሲል ቢቢሲ ዘገበ በማለት ያቀረበው ዜና ፍጹም ሐሰት እና እኛን የማይገልጽ ነው ብሏል ቢቢሲ።

ቢቢሲ አክሎም ትግራይ ቲቪ በቅርቡ፤ ከወራት በፊት “በዘጋቢያችን ቃልኪዳን ይበልጣል የቀረበን የድምጽ ቅጂ ቆርጦ በማውጣት ለዚህ ዘገባው ተጠቅሞበታል፤ ነገር ግን ቢቢሲ ይህን የመሰለ ዘገባ ፈጽሞ አልሰራም” ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለ2019 የኖቬል የሰላም ሽልማት የበቁት ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መውሰድ በጀመሯቸው እርምጃዎችና በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም በማውረዳቸው እንደሆነ በሽልማቱ ወቅት ተገልጿል።

በተመሳሳይ የቀድሞው የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለዓለም አቀፉ የሰላም የኖቬል ሽልማት አይመጥኑም” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም የኖርዌይ የሽልማት ኮሚቴ በጉዳዩ እየተነጋገሩበት እንደሆነ ገልጸው ለሰሩት ስራ አይገባቸውም እንዲያውም ሊጠየቁበት ይገባል ሲሉ ተመሳሳይ የሀሰት ፕሮፓጋንዳቸውን አሰራጭተዋል።

ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን የትግራይ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሀላፊ የሆኑት አቶ ሀዱሽ ካሱ በስልክ ተጠይቀው “ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም” በማለት ተናግረዋል።

የዝግጅት ክፍላችን ለሃላፊው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃንን የመቆጣጠር ሀላፊነት የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ ቢያነሳላቸውም እኛ አንቆጣጠራቸውም የሚል መልስ ከመስጠታቸውም በላይ አሁንም ተመሳሳይ የሀሰት ዘገባዎች እርሳቸው በሚመሩት ቢሮ መሰራጨቱ እንደቀጠለ ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.