Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ክልልን መልሶ የማቋቋም መርሐ-ግብር ተነድፎ ወደ ተግባር ተገብቷል፦ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን ሕግ የማስከበር እርምጃ መጠናቀቅን ተከትሎ በአፋጣኝ የመልሶ ማቋቋም መርሐ ግብር በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

በቅርቡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን ለመደገፍ በብሪታኒያ ለሦስት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው የበይነ-መረብ የገቢ ማሰባሰበያ ዝግጅት ተጠናቋል።

በዝግጅቱ መጠናቀቂያ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፣ መንግሥት ላለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሂደት ውስጥ መግባቱን አስታውሰው፣ በሌላ በኩል መንግሥት በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ እያካሄደ ያለው ሪፎርም ባልተዋጠላቸው የውስጥ እና የውጭ አካላት በተገመደ ሴራ ሕዝባቡ ለችግር እና ለጥፋት ሲዳረግ ቆይቷል።

መንግሥት ክህደት በፈፀሙ ኃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሕግ ማስከበር እና ሀገርን የመታደግ ተግባር ማከናወኑን በመጥቀስም፤ በተደረገው ሁለገብ ርብርብ ጁንታው ፈጽሞ በማያገግምበት ሁኔታ ግብዓተ መሬቱ ተጠናቋል፤ ርዝራዦቹም በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው ብለዋል አቶ ደመቀ።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲዎች አስተባባሪነት በዚህ መልኩ ወገኖቻቸውን ለመደገፍ እና ለማቋቋም የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባር በማካሄዳቸው አመስግነዋል።

መንግሥት ዳያስፖራው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገር ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች እና ተቋማት የማደራጀት ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመው፥ ዳያስፖራው በሰላም ግንባታ፣ በማህበራዊ ዘርፍ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በቱሪዝም በተናጠልም ሆነ በጋራ የሃገሪቱን እድገትና ብልፅግና በመተባበር እንዲያፋጥን ምቹ ሁኔታዎች መፈጥራቸውንም ገልፀዋል።

ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ለመንግሥት አስፈላጊ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታት ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ በመላክ የጥቁር ገበያን የገንዘብ ዝውውር ለማምከን በሚደረገው ጥረትም የበኩላቸው ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው፥ በብሪታኒያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል ሀገራቸውን ለመደገፍ የገንዘብ ፣ የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰው አሁንም የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አመስግነዋል።

የዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላም ዳዊት በበኩላቸው የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲቻል መንግሥት የዳያስፖራ ኤጀንሲ በማቋቋም ከሴክተር ተቋማት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.