Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ክልል ህዝብ ሰላሙን ለማናጋት ከሚሰሩ ሃይሎች ራሱን ሊጠብቅና ሊታገላቸው ይገባል- ዶክተር ሙሉ ነጋ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ህዝብ ሰላሙን ለማናጋት ከሚሰሩ ሃይሎች ራሱን ሊጠብቅና ሊታገላቸው እንደሚገባ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ገለጹ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የትግራይ ክልል ህዝብ የተለያዩ የሃሰት አሉባልታዎችን እየነዙ ሰላሙን ሊያናጉ የሚሞክሩ አካላትን ሊታገላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ህዝቡ “በሬ ወለደ” ወሬዎችን እያናፈሱ ሰላሙን ለማናጋት ከሚሰሩ ሃይሎች ራሱን ሊጠብቅና ሊታገላቸው ይገባልም ነው ያሉት።

በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የትግራይ ክልል የተረጋጋ መሆኑን ያሥረዱት ዋና ስራ አስፈጻሚው ህዝቡ ምንም አይነት ስጋት እንዳይገባው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ትናንት በሙስናና በዝምድና ህዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬም በሌላ ተግባር ወንጀል የሚፈጽሙ ከሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ህዝብ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከዴሞክራሲውም ሆነ ከልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን የህወሓት ቡድን የራሱ መጠቀሚያ ሲያደርገው መቆየቱን አስታውሰዋል።

በመሆኑም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለትግራይ ህዝብ እውነተኛ ዴሞክራሲ እና ተጠቃሚነት ለመስራት ዝግጁ በመሆኑ ህዝቡ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ወንጀለኛውን የህወሓት ጁንታ ይዞ ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ህዝቡ እንዲተባበር ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.