Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከመቐለ ከተማ ወጣቶች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ ከመቐለ ከተማ ወጣቶች ጋር ተወያይቷል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚያደርገውን ውይይት አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና የመቐለ ከተማ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ሃይለስላሴ ተሳትፈዋል፡፡

ወጣቶቹ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቀረቧቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች በተጨማሪ ባለፉት ጊዜያት በህወሓት ይደርስባቸው የነበረውን የተለያየ ጫና አንስተዋል፡፡

የከተማዋ ወጣቶች ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ይታይ የነበረውን ኢ-ፍትሓዊ የሆነ አሰራር ኮንነዋል፡፡

እንዲሁም ለውጡንም ለዓመታት ሲጠብቁት የነበረ መሆኑን በመጥቀስ የሐሳብ ነጻነት መታፈን ይደርስባቸው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

የስራ አጥነት እና ኢ-ፍትሓዊ ተጠቃሚነት የተነፈጉበት ጊዜ ዳግም ተመልሶ እንዳይመጣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል፡፡

ለወጣቶቹ ምላሹን የሰጡት ዶክተር ሙሉ ነጋ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ካለፈው ስህተት በመማር ማንንም ሳያገል ወጣቶቹን ማዕከል አድርጎ ይሰራል ብለዋል፡፡

ዶክተር ሙሉ ለውጡ ወገናዊ፣ አድሎዋዊ እና ቤተሰባዊ አሰራሮችን ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኑን ነው ያረጋገጡት፡፡

ዶክተር አብርሃም በበኩላቸው አሁን በትግራይ የመጣው ለውጥ ከምንግዜውም በላይ ለኢትዮጵያና ለክልሉ አንድነት፣ ሰላምና ልማት የመጣ ለውጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ የተገኘው ድል የመላው ትግራዋይ ድል ነው በማለት ነው አክለው የገለጹት፡፡

የመቐለ ከተማ ከንቲባ አቶ አታክልቲ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በከተማዋ እየተስተዋለ ያለውን ዝርፊያ ለማስቆምና ህዝቡም ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወጣቶች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ከንቲባው የከተማዋ ወጣቶች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን በመቆም ሰላማቸውን እንዲያስጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

በምስክር ስናፍቅ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.