Fana: At a Speed of Life!

የንግዱ ማህበረሰብ ህግን አክብሮ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግዱ ማህበረሰብ በህግን አክብሮ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት  ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ነጋዴዎች  ጋር ውይይት አካሂደዋል ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ  በነበረው ስርዓት በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ በፍትሀዊነት እንዳይሰራ ፣የአንድ ወገን ተጠቃሚነት የነበረበት ፣በአቋራጭ  የመክበር እና የአየር ባየር ንግድ እንቅስቃሴ እንደነበረ ገልፀዋል።

ነገር ግን  ነጋዴዎች ውጣውረዶችን በመጋፈጥ ለህብረተሰቡ ግልጋሎት እና ለከተማዋ እድገት ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል ።

በንግድ ስርዓቱ በኩል የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ተፈተው የነጋዴው ማህበረሰብ በተረጋጋ እና ህግን አክብሮ እንዲሰራ በማድረግ በኩል የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ።

በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ እና የንግድ ህጋዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እና ምርት የሚደብቁ ህገወጦች ላይ ለሚወሰደው እርምጃ የንግዱ ማህበረሰብ አስፈላጊውን እገዛ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ነጋዴው ማህበረሰብ የከተማዋ ኢኮኖሚ እንዲያድግ  በአካባቢው የልማት እንዲፋጠን የራሱን አስተዋጽኦ እየተወጣ ፤በቀጣይም የሚያደርጉትን ተሣትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለፃቸውን ከከተማ ፕሬስ ሴክረቴሪያት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የንግድ ስርዓቱ በአግባቡ እንዲተገበር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እንዲወስድ በውይይቱ የተሳተፉ ነጋዴዎች ጠይቀዋል ።

“በተደራጀ የነጋዴዎች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ብልጽግና ተምሳሌት እናድርግ “በሚል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ነጋዴዎች ተሣትፈዋል ።

ከውይይቱ  በኋላም የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ከነጋዴዎች ፎረም እና ከአዲስ አበባ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.