Fana: At a Speed of Life!

የኖቤል ሽልማቱ ለተቋሙም ሆነ ለዲፕሎማቶች ተጨማሪ አቅምን ይፈጥራል – አቶ ነብያት ጌታቸው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያገኙት የኖቤል ሽልማት እንደተቋምም ሆነ ለዲፕሎማቶች ተጨማሪ አቅምና ብርታትን የሚፈጥር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ተናገሩ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ቃል አቀባዩ እንዳሉት፥ ሽልማቱ ለተቋሙም ሆነ በተቋሙ ስር ለሚገኙ ዲፕሎማቶች ስራ ልዩ አቅምና ብርታትን የሚፈጥር ነው።

በዋናነት ደግሞ ኢትዮጵያ በቀጠናው የምትከተለው የጎረቤት ሀገራትን ሰላምና መረጋጋት ግምት ውስጥ የከተተ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘበት ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል የተያዘው አቋም ትክክለኛነቱን ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ትታወቅበት ከነበረው ገጽታ አንጻር ሃገሪቱን የማስተዋወቁ እንቅስቃሴ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ፈተና እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያገኙት የሰላም ኖቤል ሽልማት ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ በገንዘብ የማይተመን የመተዋወቅ እድልን እንዳስገኘም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ከገጽታ ግንባታ ባሻገር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይበልጥ ስለ ኢትዮጵያ እንዲጠይቅና እንዲያውቅ የሚያደርግ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ ይህም ለሀገሪቱ ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንቨስትመንት መነቃቃት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

ሽልማቱ በሌሎች የዓለም ሃገራት ዘንድ ሰላምን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ተፈላጊነት እና ተቀባይነት እንደሚጨምረውም አስረድተዋል።

በትእግስት አብርሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.