Fana: At a Speed of Life!

የአማራና የአፋር ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ መድረክ ተጀመረ 

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፋርና አማራ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀመረ።

በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ የአፋር ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አወል አርባ “የአፋር እና የአማራ ሕዝቦች ሥነ ልቦናዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ጅማሮ ከሉሲ ዘመን ይቀድማል” ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ አብሮ በሚኖር ማኅበረሰብ ቀርቶ በቤተሰብ ውስጥ እንኳን ግጭት ተፈጥሯዊ መሆኑን በማመላከት አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ግጭቶችን በማኅበራዊ መስተጋብሮቹ የመፍታት አቅም ያላቸው ህዝቦች እንደመሆናቸው የአሁኑ የሁለቱ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት መድረክ ዓላማው ይህንኑ ማጠናከር እንደሆነ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ “መልከ ብዙ ችግሮቻችን እየፈታን እና የሚፈጠሩ ክፍተቶችን እየሞላን ከቀጠልን የማንወጣው ፈተና፣ የማናልፈው መሰናክል እና የማይናድ የጥላቻ ግንብ አይኖርም” ሲሊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንደ አብመድ ዘገባ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቱ የተለያዩ ጥናተዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ለሁለት ቀናት ይቀጥላል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.