Fana: At a Speed of Life!

የአማራን ሕዝብ ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለመ የተደራጀ ሥልጠና ሊሰጥ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራን ሕዝብ ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለመ የተደራጀ ሥልጠና ሊሰጥ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ከግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት የጦር መሳሪያ ምዝገባ እንደሚካሔድ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።
ከዚህ በፊት ያልተመዘገበ ማንኛውም የጦር መሳሪያ የታጠቀ ግለሰብ በአካባቢው በሚገኙ የምዝገባ ማዕከላት በመገኘት እንዲያስመዘግብ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አሳስቧል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለአሚኮ እንዳስታወቁት÷ የጦር መሳሪያ ምዝገባው የአማራን ሕዝብ ደኅንነት ለማስጠበቅ እና አጋዥ ኃይል ለማጠናከር ያለመ ነው።
አሸባሪው የህወሓት ቡድንና የጥፋት መንገድ ተጋሪዎች የአማራን ሕዝብ አንድነት ለመሸርሸር በብሔርና በሃይማኖት ሽፋን የተለያዩ አጀንዳዎችን እየዘረጉ መሆኑን ያነሱት ቢሮ ኃላፊው÷ የሽብር ቡድኑ አሁንም ወደ ዳግም ጦርነት ለመግባት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ በተጨባጭ እያሳየ ነው ብለዋል።
የጥፋት ኃይሉን ዓላማ ለማክሸፍ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይል በተጨማሪ ማንኛውም የጦር መሳሪያ ያለው ምዝገባ ካካሄደ በኋላ የተደራጀ ሥልጠና እንዲወስድ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ÷ ሕዝባችን ዳግም ለወያኔ ወረራ እና ጥቃት እንዳይዳረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደወትሮው ሁሉ የፀጥታ መዋቅሩ እና ደጀኑ ሕዝብ የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆን ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.