Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን “አሚኮ ኅብር” የተሰኘውን አዲስ ቻናሉን መደበኛ ስርጭት አስጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን “አሚኮ ኅብር” የተሰኘውን አዲስ ቻናል በ11 ቋንቋዎች መደበኛ ስርጭቱን በይፋ ስራ አስጀምሯል።

 

ቻናሉ በአማርኛ፥ ኦሮምኛ ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ኽምጣና፣ ጉምዝኛ፣ አዊኛ፡ እንግሊዝኛና በአረብኛ ቋንቋዎች መረጃዎችን ለተመልካቾች የሚያደርስ ነው ተብሏል።

 

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተጨማሪ “አሚኮ ኅብር” የተባለ አዲስ ቻናሉን ከማስመረቅ በተጨማሪ የአማራ ራዲዮ የተመሰረተበትን 25 ዓመትም እያከበረ መሆኑ ተገልጿል።

 

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ አሚኮ የሀገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ በአማራ ክልል እንዲቀጣጠል ካደረጉ ግንባር ቀደም ሚዲያዎች ቀዳሚው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

የአማራን ሕዝብ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች እንዲሁም  በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የጋራ ችግር የመፍታት ተግባሩን ተቋሙ ሊያሳድግ ይገባልም ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

 

የአሚኮ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ የሽጥላ በበኩላቸው ÷ በአማራ ክልል ሕዝባና መንግስት ላይ ቀደም ሲል የተሰሩትን አፍራሽ  ሴራዎች  በማክሸፍ በክልሉና በሀገሪቱ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታን በመፍጠር የተተከለውን የሀሰት ትርክት መንቀል ያስፈልጋል ብለዋል።

 

የጋራ ሀገር  የመገንባት ሂደት ላይ ስለችግሮቻችን በጋራ ለመምከርና በጋራ ለመቆም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በጀመረው ስራ ግንባር ቀደም መሆን ይኖርበታልም ነው ያሉት።

 

በሀገር ግንባታ፣ በህብረተሰብ ግንባታ እና በወንድማማችነት ግንኙነት ግንባታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የዘመነ ሚዲያ መገንባት ወሳኝ በመሆኑ በሁሉምመንገድ ይሄንን ሚዲያ መደገፍ ይኖርብናል ሲሉም  አሳስበዋል።

 

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥዬ እንዲሁ፥  አሚኮ በተለያዩ  ቋንቋዎች ተጨማሪ ቻናል ማስጀመሩ ኀብረ  ብሔራዊ ወንድማማችነትን ለማሳደግ እና የተዘሩ የሀሰት ትርክቶችን ለማጥፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

 

ተቋሙ በአጠቃላይ በሚኖሩት 11 የስርጭት ቋንቋዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃዎችን ለማድረስ እንደሚተጋም ጠቁመዋል።

 

 

በመርሐ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የመገንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እናሌሎች የፌደራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ ግለሰቦችም ተገኝተዋል።

 

ዛሬ መደበኛ ስርጭቱን የጀመረው “ አሚኮ ኅብር” የቴሌቪዥን ጣቢያ በኢትዮ ሳት እንደሚሰራጭ ታውቋል።

 

በይስማው አደራው

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.