Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አፀደቀ።
ምክር ቤቱ በወቅታዊ የሀገሪቱ እና የክልሉ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የክልሉ ሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ያቀረበውን ሪፖርት ያደመጠው የህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ቀርቦ መፅደቁን አብመድ ዘግቧል።
ቋሚ ኮሚቴው የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ሰላም በአሰተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ባላቸው ነጥቦች ላይ ቀርበው የነበሩ የውሳኔ ሃሳቦችም÷
1 የአማራ ክልል መንግስት የክልሉ ህዝብ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ ጥፋት በፈፀሙ የጥፋት ሃይሎች ላይ ህግ ለማስከበር የወሰደውን እርምጃ እና በክልሉ ውስጥ የተገኘውን ሰላም በአዎንታ የሚያይ ሆኖ ከሃገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የውስጥ አቅምን በማጠናከር ህግ የማስከበሩ ስራ መቀጠል ይኖርበታል።
2. የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በመጣሉ የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ መንግስት (አስተዳደር) እንዲቋቋም የወሰነውን ውሳኔ በመደገፍ የውሳኔ ሃሳብ ያቀረብን ሲሆን ምክር ቤቱ እውቅና እንዲሰጥ ጠይቋል።
3. የአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና የሚሊሻ ህገ ወጡ የትህነግ ቡድን የፈፀመውን ጥቃት ለመከላከል ላደረጉት ቆራጥ ተጋድሎ የክልሉ ምክር ቤት ክብር እና እውቅና እንዲሰጠውም ነው የውሳኔ ሃሳቡ ያነሳው ።
4. የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ አጥብቆ የሚያምን በመሆኑ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኝ የጠቆመው ምክረ ሃሳቡ በሚኖርበት አካባቢም ህግና ስርዓትን በማክበር እና በማስከበር ግንባር ቀደም ሚና አለው።
ሆኖም ትህነግ እና የእርሱ ተላላኪ የሆነው የኦነግ ሸኔ ቡድን ማንነትን ማእከል በማድረግ የፈጸሙውን ግድያ መንግስት እውቅና እንዲሰጥና ድርጊቱ ድጋሚ እንዳይፈፀም ብሎም ህገ መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር ከለላ እንዲሰጣቸው ሃላፊነቱን እንዲወጣ፣ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ካሳ እንዲያገኙ እና የተፈናቀሉ ወገኖችም ወደመደበኛ ቦታቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ፣ የአማራ ክልል መንግስት ከክልሉ ውጭ በሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ላይ የሚፈፀም ወከባ፣ ግድያ እና መፈናቀል እንዲቆምና ዜጎች ተረጋግተው እንዲኖሩ ከፌደራል መንግስት እና ከሌሎች ክልል መንግስታት ጋር በቅንጅት ተቀራርቦ እንዲሰራ ጉዳዩንም በአንክሮ እንዲከታተል በምክረ ሀሳቡ ላይ አመልክቷል።
5. የፌደራል መንግስት ትህነግ የፈፀመውን የክህደት ሴራ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ሀገሪቱ ከተደቀነባት አደጋ እንዲታደግ እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የመጠበቅ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና የአማራ ክልል መንግስትም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል።
6. መላው የአማራ ክልል ህዝብ ትህነግ የፈፀመውን ክህደት እንዲያወግዝ እና እየተወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ በመደገፍ ከመንግስት ጎን እንዲቆም። የጥፋት ሃይሎች በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ለመከላከል አካባቢውን ተደራጅቶ እንዲጠብቅ በሚል የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ ፀድቋል ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.