Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የጤፍና የስንዴ ሰብል ማሳን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣መስከረም 22፣2014(ኤፍ ቢሲ)የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በኩታገጠም የለማ የጤፍ እና የስንዴ ሰብል ማሳን ጎበኙ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት ሃይሌ፣ የቀድሞው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መለሰ መኮንን፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ፃዲቅን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በወረዳው የአረርቲ ዙሪያ እና ዘወልዴ ቀበሌ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች አሽኔ ሃይለማርያም፣ ደረጀ ሃይለጊዮርጊስ እና ደርሰህ በቀለ እንደገለፁት ተመሳሳይ የሰብል ዓይነቶችን በአንድ አካባቢ በኩታገጠም በመዝራት የማምረት ዘዴ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
በመኸር ምርት ዘመኑ በኩታገጠም ያለሙትን የጤፍ እና የስንዴ ሰብል በቂ ግብዓት በመጠቀማቸው አሁን በጥሩ ቁመና ላይ በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ ያደረጉት አርሶ አደሮቹ፥ ከአንድ ሄክታር እስከ 25 ኩንታል ጤፍ ሊያገኙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
የምርት ብክነት እንዳያጋጥም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በአግባቡ ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ገልፀዋል።የማጨጃ ማሽን ኮምባይነር እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከ 5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታገጠም የለማ ነው።
ከ1 ሺህ 100 ሄክታር በላይ ማሳ በኩታገጠም የስንዴ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን፥ 4ሺህ 425 ሄክታር ያህሉ ደግሞ በጤፍ ሰብል መሸፈኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪው አቶ በቀለ ወንደሰን ተናግረዋል።
ሰብሎችን በኮምባይነር ለመሰብሰብና ለመውቃት እንዲቻል ከዞኑ ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።
በወረዳው በዘር ከተሸፈነው ከ42 ሺህ ሄክታር መሬት ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 105 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል ያሉት የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት ሃይሌ፥ በ2013/14 የመኸር ምርት ዘመን 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል።
በሰላም አሰፋ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.