Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የተረጋጋና ዘላቂ ልማት ለማከናወን የሚያስችል ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እየሰራ ነው – ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የተረጋጋና ዘላቂ ልማት የሚከናወንበትና ዜጎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት ወጥተው የሚገቡበት እንዲሆን ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በክልሉ ህዝብን እርስ በእርስ በማጋጨት ፣በመከፋፈልና ሰላሙን በመንሳት በልማት ስራ ላይ አተኮሮ እንዳይሰራ በውስጥና በውጭ ሃይሎች በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ችግሩን ለማስወገድና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ የተቀናጀ፣የተደራጀና የተናበበ ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በተለይ ሃይማኖትንና ብሄርን ሽፋን በማድረግ የህዝቡን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳዮችን በመለየት የክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ የህግ ማስከበር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በድርጊቱ ውስጥ እጃቸውን በማስገባት እየሰሩ ያሉ አካላትን በመለየት በቁጥጥር ስራ የማዋል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቆመዋል።

እየተደረገ ያለው ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስት ህዝቡን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቅ አቅም እንዳለው ጠቅሰው ከዚህ በተጻራሪ በጦር መሳሪያ ጭምር ታጅበው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስገንዝበዋል።

የጸጥታ ሃይሉ በየአከባቢው እያከናወነ ለሚገኘው የህግ ማስከበር ስራ የክልሉ ወጣትና መላው ህብረተሰብ የበኩሉን እንዲወጣ ማሳሰባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.