Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካው ኦሪዮን የሳተላይት ኩባንያ በዘርፉ ልማት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ “ኦሪዮን አስት” ከተሰኘ የአሜሪካ የሳተላይት ኩባንያ ባለቤትና ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር አልቪን የተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም በሳተላይት መረጃ አጠቃቀምና በህዋ ቴክኖሎጂ ልማት ላይ በትኩረት መምከራቸው ተገልጿል፡፡
 
ሚስተር አሌክሳንደር አልቪን ድርጅታቸው በስፔስ ቴክኖሎጂ፣ በሳተላይት ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
 
ኩባንያቸው በህዋ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የሰው ሃይል ልማትና ኢንቨስትመንት አተኩሮ የሚሰራ እንደሆነና፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተቀራርበው ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አብራርተዋል፡፡
 
ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ በመስራት ሁለት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ወደ ህዋ መላኩዋን አውስተው÷ የስፔስ ኢንዱስትሪውን አቅም በመጨመር አገራዊና አህጉራዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሚናዋን ለመወጣት ፍላጎት አላት ብለዋል፡፡
 
በውይይቱ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ አቅም የሚሆን የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያ ማዕከል መገንባቷን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የስፔስ ቴክኖሎጅ ማዕከል ለማድረግም በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ እና በሰው ሃብት ልማትና የሳተላይት መረጃን አመንጭቶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ስርዓት እየተገነባ ነው ተብሏል፡፡
 
መሰል ዓለም አቀፍ የህዋ ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ጋር በጥምረት መስራት እንፈልጋለን ያሉት ሚኒስትሩ ÷ በቀጣይ የዘርፉን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የትብብርና ድጋፍ ማእቀፎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ለይቶ የሚያቀርብ ቡድን የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.