Fana: At a Speed of Life!

የአረቡ ዓለም ስለ ህዳሴ ግድብ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በአረብኛ ቋንቋ የሚሰሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል -ፕሮፌሰር አደም ካሚል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረቡ ዓለም ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በአረበኛ ቋንቋ የሚሰሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ የታሪክ ጸሃፊና የኢትዮ አረብ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ተናገሩ።
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ኢትዮጵያ ላይ ስለተጋረጡ ወቅታዊ የውጭ ጫናዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የአረቡን ዓለም በቂ ግንዛቤ ለማስያዝ በአረብኛ ቋንቋ የሚሰሩ የሚዲያና ኮሙንኬሽን ስራዎች መጠናከር አለባቸው ሲሉም ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ የያዘው ዓላማ፣ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌላው ለአረቡ ዓለም በሰፊው ለማስገንዘብ ጉባኤዎችን ጨምሮ የተለያዩ ኩነቶችን በአረብኛ ቋንቋ ማዘጋጀት ጠቃሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርጉት ጥረት ግድቡ የታችኛው ሃገራትን እንደሚጎዳ አስመስሎ ማቅረብና በግድቡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ ጣልቃ ለመግባት በመሞከር በግንባታው ላይ ሌሎች እምነት እንዳይኖራቸው እስከማድረግ ይደርሳል ነው ያሉት።
ለዚህም ከ4 ሺህ በላይ የመገናኛ ብዙሃንን እንደሚጠቀሙ የተናገሩት ረ/ፕሮፌሰሩ፥ ይህንን ፕሮፖጋንዳ ለመቀልበስ በአረብኛ ቋንቋ የሚተላለፉ መልዕክቶችንና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረቱ መምጣታቸውን በማንሳት ምክንያቶቹንም አብራርተዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን እየሆነ ሲመጣ በተለይም ግብፅና ሱዳን ለማስተጓጎል የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ረዳት ፕሮፌሰር አደም ገልጸዋል።
የግድቡ እውን መሆን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ መስክ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ግብፅና ሱዳን የማሰናከል ሴራቸውን ቀጥለውበታል ነው ያሉት።
ግንባታው ሲጀመር ኢትዮጵያ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳታገኝ ከማድረግ ጀምሮ እስከ ዛቻና ማስፈራሪያ፣ ውስጣዊ ሰላም እንዳይኖራት መስራታቸውንም አስታውሰዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የገጠማትን ጫና ለመቋቋም ከምንም በላይ አንድነትን ማጠናከር፣ መተባበርና በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።
“ኢትዮጵያ በታሪክ ቀኝ ያልተገዛች፣ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት በመሆኗ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው” ያሉት ረዳት ፕሮፈሰር አደም ካሚል “በዲፕሎማሲውም አሸናፊ በመሆን ታሪክ መስራት ይገባል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ሁለንተናዊ ጫና እስካሁን የከሸፈው በኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያን እውነት በሚረዱ ሃገራት ድጋፍ መሆኑንም አንስተዋል።
በቀጣይም ይህን ጫና ለመቀልበስ ከኢትዮጵያ የሚጠበቀው ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከርና ደጋፊ ሃገራትን በማስተባበር መንቀሳቀስ መሆኑን አብራርተዋል።
ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያን ደካማና የተከፋፈለች አድርጎ በመሳል ሃገሪቱ በሌላው አለም ዘንድ ያላትን ስምና ልዕልና እንድታጣ ለማድረግ ከሚጠቀሙበት ፕሮፖጋንዳ አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማሲው ዘርፍ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እውነታዎች በሚረዱ አፍሪካዊያንና ሌሎች አገራት ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 82 በመቶ የደረሰ ሲሆን በቅርቡ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
0
People Reached
128
Engagements
Boost Post
119
5 Comments
4 Shares
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.