Fana: At a Speed of Life!

የአብሮነትና የወንድማማችነት ገመዶችን ይበልጥ በማጠናከር በሕዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት ስር እንዲሰድ መስራት ያስፈልጋል-አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ አዲሱን አመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሊጠናቀቅ አንድ ቀን በቀረው ዓመት ዓለም አቀፋዊ ከሆነው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ተጨምረውበት እቅድ አፈጻጸሞቻችንን ከባድ ቢያደርጉም ያጋጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍትሓዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስኬቶችን የተመዘገቡበት አመት ነበር ብለዋል፡፡

የሸገር ፓርክና የእንጦጦ ፕሮጀክት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ የግብርና ምርትና ምርታማነት የማሳዳግ ሥራ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ አመት የውሃ ሙሌት የተከናወነ አመት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከባድ የመገናኛ ብዙሃን እና ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት እየታወጀብን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቃችን በአንድነት ስንቆም የማንሻገረው እንቅፋት እንደማይኖር ያሳየንበት እና የአይቻልም መንፈስ ሰብረን መቻላችንን ለአለም ያበሰርንበት ዓመት ነበር ነው ያሉት፡፡

አፈ ጉባኤው በሌላ በኩል ባለፉት አመታት የኢትዮጵያ ህዝቦች በየአከባቢያቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የማድረግ እና በመሰረተ ልማት ግንባታ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

ሆኖም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት ርዕይ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር በመሆኑ ለዘመናት አስተሳስረውን የኖሩ የአብሮነትና የወንድማማችነት ገመዶችን ይበልጥ በማጠናከር በሕዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት ስር እንዲሰድ ከሁሉም ዜጋ ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ እንገኛለንም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት አብረን የኖርን፣ በርካታ የጋራ እሴቶች ያሉንና ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን፣ ከሚያራርቁን ይልቅ የሚያስተሳስሩን እሴቶች በብዙ እጥፍ ይልቃሉ ማለታቸውን ከፌዴረሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በመሆኑም ለሀገር ህልውና፣ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለዜጎችና ለሀገር ሰላም፣ ለህግ የበላይነት እና ለጋራ ብልጽግና በአንድነት መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የሕገ መንግስቱ የበላይነት እንዲረጋገጥና የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ፣ በሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች የተመጣጣነ እድገትና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲረጋገጥ እና በሕዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተ አገራዊ አንድነት እንዲዳብር ከምንጊዜዉም በላይ የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

አዲሱ ዓመት ብዝሃነትን በአግባቡ የሚስተናግድበት፣ የጋራ እሴቶች የሚጎለብቱበት፣ ከመበታተን ወደ መሰባሰብ የሚወስድ እና የሠላም፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የመተሳሰብ እና የብልጽግና ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.