Fana: At a Speed of Life!

የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ ምርቶች በውጪ ሀገር ገበያ ተፈላጊነታቸው መጨመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶች በውጪ ሀገር ገበያ ተፈላጊነታቸውና ተወዳዳሪነታቸው እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለሰ እንደተናገሩት÷ በአዲሱ በጀት ዓመት 32ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ሀገር የገበያ ትስስር ለአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ለመፍጠር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በዚህም 250 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች የምርት ናሙናዎችን በማስተዋወቅና በቀጥታም ሆነ ከላኪዎች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ ከውጭ ሀገር ገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ባሳለፍነው በጀት ዓመት 27 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የተለያዩ ማኑፋክቸሪንግ ምርት ውጤቶች ወደ ውጭ ሀገር ገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ ታቅዶ 50 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር የሚሆን የገበያ ትስስር መፈጠር መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 141 የሚሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ሀገር ገበያ ተጠቃሚ እንደነበሩም ጠቁመዋል፡፡

ወደ ውጭ ከተላኩ ዋና ዋና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች መካከል የኬሚካልና ማዕድን፣ የዕደ-ጥበብ፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና የአግሮፕሮሰሲንግ ምርቶችን ይገኙበታልም ነው ያሉት፡፡


አቶ አሸናፊ እንደሚሉት አፈፃፀሙ ከእቅድ አንፃር የተሻለ ሲሆን÷ ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው የዘርፉ የማሽነሪና የፋይናንስ አቅርቦት በመሻሻሉ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠናዎች በመጠናከራቸው የሃገራችን ምርቶች በውጪ ሀገር ገበያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳዳሪነታቸውና ጥራታቸው እየጨመረ በመምጣቱ እና የሽያጭ ዋጋቸውም በዚያው ልክ በመጨመሩ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትን በውጭ ገበያ ለማስተዋወቅ የምርት ናሙናዎች ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መላኩንም ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.