Fana: At a Speed of Life!

የአካል ጉዳተኞችን የእኩል ዕድል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የተጠቃለለ ሕግ እየተዘጋጀነው-ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የአካል ጉዳተኞችን የእኩል ዕድል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

የአካል ጉዳተኞች ቀን በዛሬው እለት “አካል ጉዳተኞችን አካታች፣ ምቹና ዘላቂ የተሻለ ዓለምን በድህረ ኮቪድ-19 እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ መከበር ጀምሯል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ በመሪ ቃሉ የተካተቱ አካል ጉዳተኞችን የሚያካተት፣ ምቹ መደላድል የሚፈጥር እና በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት መዘርጋት፤ በተግባርና በተጨባጭ ልናሳይ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የአካል ጉዳተኛ ዜጐች መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ፣ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት መብትና ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን አዋጅ፣ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች የድርጊት መርሃ ግብርና የአካላዊ ተሃድሶ ስትራቴጂ፣ ለአካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ የማስገባት መመሪያ መውጣቱንም በማሳያነት አቅርበዋል።

በአሁኑ ጊዜም በአካል ጉዳተኞች የመብት ጥሰት ለመከላከል እና የእኩል ዕድል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዘውን የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ በበኩላቸው፥ አካል ጉዳተኛ የመሆን አጋጣሚ ከፅንሰት እስከ ህልፈት ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የሚገኝ በመሆኑ ለአካል ጉዳት መከሰት መንስኤ የሚሆኑ ችግሮችን ለመቀነስ በችግሩ ልክ ማሰብና በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በዓሉ በብሔራዊ ደረጃ በባህር ዳር ከተማ ታህሳስ 17 እና 18 ቀን 2ዐ13 ዓ.ም በማክበር እንደሚጠናቀቅ ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.