Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት ለሁለተኛ ጊዜ የለገሰው ሰብዓዊ ድጋፍ መቀሌ ደረሰ

አዲስ አበባ፣መስከረም 27፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለሁለተኛ ጊዜ የለገሰው ሰብዓዊ ድጋፍ መቀሌ መድረሱን ብሄራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በትግራይ ክልል በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች የሚሆን የሰብዓዊ ድጋፍ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በአየርና በየብስ መጓጓዙን  አስታውቋል።

የአውሮፓ ህብረት ለሁለተኛ ጊዜ የለገሰው የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁሶች መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ መድረሳቸውን የጠቆመው ኮሚሽኑ ፥ ድጋፉ በትናንትናው እለት መቀሌ መድረሱን ገልጿል።

ድጋፉም በዋናነት የምግብና የህክምና ቁሳቁስ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።

እስከ መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኮሚሽኑ እውቅና መሰረት በትግራይ ክልል ለሚንቀሳቀሱ 44 የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች ስራ ማስኬጃ የሚውል ከ286 ሚሊየን ብር በላይ ወደ መቀሌ መጓጓዙን አስታውቋል።

በተመሳሳይ እስከ መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ የተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች 686 ድጋፍ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች  ወደ መቀሌ ማጓጓዛቸውንም ጠቁሟል።

ከዚህም ውስጥ እስካሁን ባለው ሂደት 122 ከባድ ተሽከርካሪዎች መመለሳቸውን ነው መግለጫው ያመለከተው።

ድጋፉም በዋናነት 18 ሺህ 812 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ እና 6 ሺህ 225 ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሁም 759 ሺህ 235 ሊትር ነዳጅ መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ አመልክቷል።

ለአርሶ አደሩ የሚሆን 1 ሺህ 36 ሜትሪክ ቶን ምርጥ ዘር መጓጓዙም እንዲሁ።

ተጨማሪ ነዳጅ የጫኑ 10 ከባድ ተሽከርካሪዎች ሰመራ መድረሳቸውና በቀጣይ ጊዜያት ወደ መቀሌ እንደሚጓዙም ገልጿል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ወደ መቀሌ የሚያጓጉዟቸውን የሰብዓዊ ድጋፎች እንቅስቃሴንእያስተባበረ እንደሚገኝም አስታውቋል።

የዓለም የምግብ ድርጅትና የካቶሊክ ተራድኦ አገልግሎት የሚመራቸው ድርጅቶች ድጋፉን በትግራይ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች እያከፋፈሉ መሆኑንም ነው የጠቆመው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.