Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት በቅድመና ድህረ ምርጫ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ከመታዘብ ባለፈ በቅድመና ድህረ ምርጫ ወቅት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።
 
የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ተወካዮች ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር በ2012ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ተወያይተዋል።
 
ተወካዮቹ ለሀገር አቀፉ ምርጫ እየተካሄደ ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሁለት ሳምንታት ምልከታ አድርገዋል።
 
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ፥ እየተካሄደ ስላለው የፖለቲካ ለውጥ በተለይም ለሃገር አቀፉ ምርጫ እየተደረገ ስላለው ቅደመ ዝግጅት ለፓርላማ አባላቱ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
 
በዚህም ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሰራ እንደ አዲስ ከማደራጀት ጀምሮ ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አላሰራ ብለው የነበሩ ህጎች ተሻሽለው በምክር ቤቱ እንዲጸድቁ መደረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
 
ሀገር አቀፍ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሰላምና ጸጥታ ተቋማት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ተቋማት ከወዲሁ ቀድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ያነሱት ምክትል አፈ ጉባዔዋ፥ የአውሮፓ ህብረት በዚህ ላይ ያለውን የካበተ ልምድ እንዲያካፍል ጠይቀዋል።
 
የህብረቱ የፓርላማ አባላት ልዑክ ቡድን መሪ ሎዊ ዴፋይ በበኩላቸው፥ የአባላቱ የመስክ ምልከታ ትኩረት ህብረተሰቡ ስለ ምርጫና የምርጫ ታዛቢዎች ያለው ግንዛቤ፣ የሀገሪቷ የፖለቲካና የሰላም ሁኔታ፣ የትራንስፖርት፣ የምርጫ መሳሪያዎች አቅርቦትና ሌሎችም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
 
ከዚህ ባለፈም ከምርጫው ጋር ግንኙነት ካላቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውን ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል።
 
የልዑክ ቡድኑ የሲቪክ ማህበራት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ውይይት ማድረጉንም አስረድተዋል።
 
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የፓርላ አባላቱም ሆኑ የጸጥታ አካላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
 
ህብረቱ በመጭው የካቲት ወር መጨረሻ ላይ ታዛቢ መላክ አለመላኩን ያሳውቃል ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.