Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር በትግራይ ክልል ያደረገው ምልከታ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፍላጎት እና ጽኑ አቋም ያሳየ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር በትግራይ ክልል ያደረገው ምልከታ ኢትዮጵያ ለሰላም እና ሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ ያላትን ፍላጎት እና ጽኑ አቋም ያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸውን አንስተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከቻይና ጋር የነበረው ምክክርም ስኬታማ እንደነበር ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።
ቻይና ከአገራቱ ጋር በሰላም እና ልማት በጦር መሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በመሰረተ ልማት እና በመሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው በኩል በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገር ውስጥ የመመለስ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አምባሳደር ዲና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ገልጸው÷ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በህብረቱ በኩል የወጣው መግለጫ ለአንድ ወገን ያዳላ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የምትከተለውን ፍትሃዊ የውሃ ሃብት አጠቃቅም መርህ የታችኞቹን ሃገራት በማይጎዳ መልኩ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
የአባይን ወንዝ በተመለከተ የአውሮፓ ህብረት ለግብጽ በወገነ መልኩ ያወጣውን መግለጫ እንዲያጤነውም አምባሳደር ዲና ጥሪ አቅርበዋል።
በሶስትዮሽ ድርድሩ የአውሮፓ ህብረት በታዛቢነት ሲሳተፉ መቆየቱም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በወንደወሰን አረጋኸኝ እና በለይኩን አለም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.