Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ በኢትዮጵያ የኅብረቱ ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ገለጹ።
 
አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
በተለይም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ ተከትሎ ኅብረቱ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
 
ይህን ተከትሎም የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ሥምምነት በፈረንጆቹ 2016 መፈረሙንና ሥምምነቱን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የወቅቱ የአውሮፖ ኅብረት ፕሬዚዳንት ጃን ክላውድ ጁንኬ ናቸው በቤልጂየም የተፈራረሙት።
 
ሥምምነቱም የጋራ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን በጋራ እልባት ለመስጠትና የሁለትዮሽ ስትራቴጂካዊ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን በማብራራት ኅብረቱ ይህ ስትራቴጂካዊ ሥምምነት በዓለም ላይ ከጥቂት አገራት ጋር ብቻ እንዳለው ጠቁመው ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስረድተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ በቀጠናው ለበርካታ ዓመታት በመንግሥታቱ ደርጅትና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በተሰማሩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ አበርክርቶ እንዳላትና ኅብረቱም ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን በፖለቲካው መስክ ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።
 
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ኅብረቱ ጣልቃ እንደማይገባ የገለጹት አምባሳደሩ ኅብረቱ የመንግሥታቱ ድርጅትና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን እሴቶች ያከብራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.