Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኀብረት በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መሻሻሉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኀብረት በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መሻሻሉን ገለጸ፡፡
የኀብረቱ የግጭት አስተዳደር ኮሚሽነር ጃኒዝ ሊነርሲስ በትግራይና ሶማሌ ክልል ያደረጉትን የሁለት ቀናት ጉብኝት ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ነው በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መሻሻሉን የገለጹት፡፡
ኮሚሽነሩ በመጀመርያው ቀን ጉብኝታቸው በትላንትናው ዕለት ወደ ሶማሌ ክልል አቅንተው በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን የገለፁ ሲሆን ፥ በድርቁ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል።
በሁለተኛው ቀን ጉብኝታቸው ዛሬ ወደ መቀሌ ተጉዘው እንደነበር የገለፁት ኮሚሽነሩ ፥ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ መሻሻል ማሳየቱን መታዘባቸውን፣ በኢትዮጵያ መንግስት በኩልም ሰብዓዊ ድጋፉ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ማስተዋላቸውን ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልል በነበራቸው ቆይታ ወደ ክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ እየገባ ያለበት መንገድ የሚመሰገን ቢሆንም፥ አሁንም በክልሉ ባለው የጥሬ ገንዘብና የነዳጅ እጥረት ሳቢያ በክልሉ ጉዳት ላይ ለወደቁ ሰዎች ድጋፉን ለማድረስ አዳጋች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ በክልሉ ባንክና መብራትን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲመለሱ መስራት አንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በትግስት ብርሃኔ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.