Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ 5 ሺህ የሚሆኑ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻህፍት አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከሰራተኞቹ እና ከአድማጭ ተመልካች የሰበሰበውን 5 ሺህ የሚሆኑ መጻህፍት ለአብርሆት ቤተ መጻህፍት አስረከበ።

“ሚሊዮን መጻህፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ ” በሚል ለአብርሆት ቤተ መጻህፍት የሚደረገው የመጽሃፍት ልገሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዛሬው እለትም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ 5 ሺህ የሚሆኑ መጻህፍትን ለቤተ መጻህፍቱ አስረክቧል።

መጻህፍቱን ያስረከቡት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በቀለ ሙለታ÷ መጻህፍት የአሁኑን ትውልድ ከሚመጣው ትውልድ የሚያስተሳስሩ እንደመሆናቸው፤ እኛም ይህን የማስተሳሰር ስራ አካል በመሆናችን ደስተኞች ነን ብለዋል።

መጽሃፍቱን የተረከቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማቲዎስ እንሰርሙ እንደገለጹት÷ የአብርሆት ቤተመጽሃፍት 4 ሚሊየን መጻህፍት ያስፈልገዋል።

አሁን ላይ ከውጭም ከሀገር ውስጥም የተለያዩ መጽሃፍት እየተበረከቱ እንደሆነና ይህም አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም የዚህ አካል በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፥ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦችም ለቤተ መጻህፍቱ የሚደረገው የመጻህፍት ማሰባሰብ አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ስራዎች በስፋት ያሏቸው እንደመሆኑ፥ መሰል ስራዎችን ለለአብርሆት ቤተ መጻህፍቱ ቢያስረክቡ ለትውልድ የሚተርፍ መሆኑን አስረድተዋል።

በሃይማኖት ኢያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.