Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ነዋሪ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ።

“ደማችን ለመከላከያ ሠራዊታችን ” በሚል መሪ ቃል የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የፍቅር በጎ አድራጎት ማህበር አባላት በዛሬው ዕለት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ የደም ልገሳ መርሃ ግብር አከናውነዋል ።

በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ፣ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና የትግራይ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል ተገኝተዋል ።

በተከናወነው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ወቅት የኩምቢ ኦይል ትሬዲንግ ፒ ኤልሲ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የ1 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ድጋፉንም ለአዲስ አበባ ብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለአቶ መለሰ ዓለሙ እና ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለዶክተር ሙሉ ነጋ አስረክበዋል ።

መከላከያ ሲመታ አይናችን እንደተመታ ነው የምንቆጥረው ያሉት የኩምቢ ኦይል ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ገ/አናንያ መከላከያን መደገፍ ኢትዮጵያን ከጥፋት ሀይሎች ማዳን ነውና የትግራይ ባለሃብቶች መንግስት የጀመረውን ህግን የማስከበር ተግባር በመደገፍ ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው  ይህ መጥፎ ታሪክ የትግራይ ህዝብን እንደማይወክለው በመግለፅ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ወጣቶች እና ባለሃብቶች በተግባር ላሳዩት የደም ልገሳ መርሃ ግብርና የገንዘብ ድጋፍ በቂ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል ።

ላበረከቱትም አስተዋጽኦ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸው ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የትግራይን ህዝብ ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ለመነጠል  የህወሓት ቡድን ለበርካታ አመታት ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ዶክተር ሙሉ ነጋ የትግራይ ህዝብ በሀገር አንድነት የማይደራደር ህዝብ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

ይህ ወቅት የትግራይ ህዝብ ነጻ የሚወጣበት እንዲሁም የልማት ፣ የዲሞክራሲ እና የሰላም ተቋዳሽ የሚሆንበት አጋጣሚ በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጊዜያዊ አስተዳደር የተጀመሩ ተግባር ጎን በመሆኑ ድጋፉን እንዲገልጸ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.