Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ የንግዱን ማህበረሰብ አስጠነቀቀ  

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በኮሮና ቫይረስ የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የዋጋ ጭማሪ እና ሌሎች ህግ ወጥ ተግባራትን ለሚፈፅሙ የንግዱ ህብረተሰብን አስጠንቅቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊአቶ አብዱልፈታህ ዩሱፍ ባስተላለፉት መልእክት፥ የኮሮና ቫይረስ መገኘት ሳንረበሽና ሳንደናገጥ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ሀይል የሚሰጠውን መረጃ በተረጋጋ ሁኔታ በመከታተል ያጋጠመንን ወረርሽኝ የምንቋቋምበትና በሽታውን የምንናስወግድበት ግዜ እሩቅ እንደማይሆን እምነቴ ጽኑ ነው ብለዋል።

በሽታው በወቅቱ የፈጠረውንና ሊፈጥር ይችላል ተብሎ የሚገመተውን አደጋ ሁሉ አብዛኛው የንግዱ ህብረተሰብ ሻጭም ገዥም እንደመሆኑ መጠን እንደማንኛውም ሰው ለአደጋው ተጋላጭ መሆኑ እሙን ነው ብለዋል አቶ አብዱልፈታህ።

ነጋዴው ህብረተሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ በያገባኛል፤ በእኔነት እና ከማንኛውም ግዜ በበለጠ ሀገራዊ ስሜት ከሸማቹ፣ ከነዋሪው ህዝብና ከመንግስት ጋር በጋራና በአንድነት በመቆም ማንኛውም ለንግድ የሚውል እቃ፣ ሸቀጥ፣ መሰረታዊ የፍጆታ እቃ፣ ምርትና አገልግሎት ላይ በምንም አይነት መልኩ እና ሁኔታ ዋጋ ሳይጨምር፣ የጥራት ደረጃ ሳያጓድል የሚዛንና የመስፈርያ መሳርያዎችን ሳያስተጓጉል፣ ባእድ ነገር ሳይቀላቅል፣ ምርት ሳይደብቅ የዜግነት ሀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ከዚህ ውጪ የኮሮና ቫይረስ ሊያደርስ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ክፉ አጋጣሚ በመጠቀም በስግብግብነት ስሜት ለንግድ የሚቀርብ ማንኛውም እቃ፣ ሸቀጥ፣ መሰረታዊ የፍጆታ እቃ፣ የፋብሪካም ይሁን የግብርና ውጤት ምርትና አገልግሎት ላይ ቀድሞ ከነበረው ዋጋ በላይ ዋጋ ጨምሮ፣ የጥራት ደረጃ አጓድሎ፣ ባእድ ነገር ቀላቅሎ፣ ምርት ደብቆ ወይም ሌላ በንግድ ስራ ላይ ተገቢ ያልሆነ ተግባር መፈፀም እንደሚያስቀጣም ገልፀዋል።

በዚህ ተግባር የተገኘ ማንኛውም ነጋዴ ላይ ቢሮው በህግ መሰረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የንግድ ስራ ፈቃዱን የሚያግድ ወይም የሚሰርዝ ወይም የንግድ ድርጅቱን የሚያሽግ መሆኑንም አስታውቀዋል።

እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ነጋዴው ላይ አግባብ ባለው ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት የሚያስቀጣና ንብረቱንም በህግ መሰረት በመንግስት የሚወረስ መሆኑን አሳስበዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.