Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ወሰነ።

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 7ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ እንዲቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አፅድቆታል።

አዲስ የሚቋቋመው የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ ተጠሪነቱ ለከንቲባው ሆኖ በቦርድ የሚተዳደር ሲሆን፥ ዳይሬክተር እና ምክትል ዳይሬክተር የሚሾምለት ይሆናልም ተብሏል።

የምክር ቤቱ አባላት የኤጀንሲው መቋቋም ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን መዘግየት እንዳልነበረበት አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በመርሃ ግብሩ በዘንድሮው ዓመት ለ600 ሺህ ተማሪዎች ዩኒፎርምን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን ያቀረበ ሲሆን፥ 300 ሺህ ተማሪዎችን ደግሞ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ አድርጓል።

የማቋቋሚያ አዋጁ መጽደቅ ከዚህ በፊት በትብብር ሲሰራ የነበረውን የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ተቋማዊ ለማድረግ እንደሚያስችል ተመላክቷል።

በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ በከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም በቀጣይ ሊሰራባቸው የሚገቡ ስራዎች መኖራቸው ተነስቷል።

ምክር ቤቱ መልካም አስተዳደርና ስራ ፈጠራን ጨምሮ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ኑሮ ውድነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው በቀጣይ ከከተማ አስተዳደሩ የተመረጡ የሁለት ቢሮዎች እና ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀምን አድምጦ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።

እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን ለማሻሻል የወጡ ረቂቅ አዋጆችን ጨምሮ ሌሎች ደንብና አዋጆችን ያፀድቃል ተብሎም ነው የሚጠበቀው።

ከዚህ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ሹመቶች ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ይፀድቃሉ።

በተስፋዬ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.