Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው መደበኛ  ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

 

 

አዲስ አበባ፣ሰኔ 8፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው አንደኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

 

የከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ እስካሁን ድረስ 1 ቢሊየን ብር መድቦ የተለያዩ  ምርቶች ወደ ከተማዋ  እንዲገቡ የተደረገ መሆኑን ገልጾ፥ አሁንም የዘይት አቅርቦት ላይ እጥረት መኖሩን ካቢኔው አፅንኦት ሰጥቶ ከተወያየ በኋላ ለዘይት አቅርቦት ብድር የሚሆን 400 ሚሊየን ብር ተጨማሪ ድጎማ መመደቡን አስታውቋል፡፡

 

በሌላ በኩል የከተማ አስተዳደሩ መሬትን ፍትሀዊ በሆነ አግባብ ለልማት ለማዋል  89 የሚሆኑ ቦታዎችን ለመኖሪያ፣ ለንግድና ለቅይጥ አገልግሎት እንዲውል የከተማውን ፕላን ባስጠበቀ አግባብ በግልፅ ጨረታ እንዲቀርቡ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

 

 

በከተማዋ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በማህበር ተደራጅተው ቤት የሚገነቡበትን አሰራር ለመወሰን በተዘጋጀ ደንብ ላይም ካቢኔው ተወይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።

 

በዚህም በከተማዋ የሚኖሩና የቤት ችግር ያለባቸውን ነዋሪዎች ችግር በሚቀርፍ አግባብ የከተማ አስተዳደሩ መሬት፣ የሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች ዲዛይን፣ ማህበራቱን የማደራጀትና ግንባታው በሚጀመርበት ጊዜ የመቆጣጠር ሀላፊነት የሚወስድ ሆኖ በማህበር ተደራጅተው የጋራ ህንጻ የሚገነቡ ሰራተኞች፣ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች፣ የፀጥታ አካላት፥ ከተደራጁ በኋላ ቁጣባ በአግባቡ መቆጠብ የሚችሉና አስተዳደሩ በሚያዘጋጀው ዲዛይን መሰረት ከፍታቸውን የጠበቁ ህንፃዎች  ለመገንባት ዝግጁ የሆኑ ወደ ግንባታ እንዲገቡ ማድረግ የሚያስችል ደንብ ላይ ተወያይቶ  ዝርዝር የአፈፃፀም ሂደቱ በከተማዋ ካለው የቤት አቅርቦት ማዕቀፍ ጋር ተጣጥሞ እንዲፈፀም ውሳኔ አሳልፏል።

 

ቀጥሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ደህንነትን ቀድሞ ለመከላከል በሚያስችል ደንብ ላይ ካቢኔው ተወያይተቶ፥ በዚህም በከተማዋ ለአደጋ ስጋት የሆኑ የህንፃ ዲዛይን ማስተካከያዎች፣ በግንባታ ላይ ያሉ ህንፃዎች ሊያሟሏቸው የሚገባ የደህንነት ጥንቃቄዎች፣ የተጠናቀቁ ህንፃዎች አጠቃቀም ሁኔታና ለቅድመ መከላከልም ሆነ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ የአደጋ መውጫ አስፈላጊውን የህንፃ ዲዛይን ማስተካከያ እንዲያደርግ ወስኗል።

 

እንዲሁም በከተማዋ የማዕድን ማውጣት ሂደት ላይ ሊሟሉ የሚገባቸው የቅድመና የአደጋ መከላከያ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት በከተማዋ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን አደጋ ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችለው ደንብ  አስፈላጊውን የአፈፃፀም ሂደት ባሟላ መልኩ ወደ ተግባር እንዲገባ ካቢኔው ተወያይቶ ማጽደቁን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.