Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጄንሲ ለበዓሉ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ማቅረቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጄንሲ ለገና በዓል የመሰረታዊ ፍጆታ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ ማቅረቡን አስታወቋል።

ኤጀንሲው ከክልል ህብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር ጥምረት በመፍጠር የግብርና ምርቶችን እያቀረበ መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ ገልፀዋል።

በዚህም ከኦሮሚያ፣ ከአማራ እና ከደቡብ ክልል የህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን፥ ጥራት እና ደረጃውን የጠበቀ ምርት እየገባ ነው ብለዋል።

ለበዓል ግብይትም ሽንኩርት በኪሎ ከ10 እስከ 12 ብር፣ ጤፍ በኩንታል ከ2 ሺህ 900 እስከ 3 ሺህ 350 ብር፣ በሬ ከ17 ሺህ እስከ 21 ሺህ ብር፣ ዘይት በሊትር ከ65 እስከ 75 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም እንቁላል ከ3 ብር ከ50 ሳንቲም እስከ 3 ብር ከ75 ሳንቲም፣ ቅቤ በኪሎ ከ225 ብር እስከ 230 ብር፣ አይብ በኪሎ ከ65 እስከ 75 ብር እንዲሁም ዱቄት በኪሎ በ10 ብር እየተሸጠ ይገኛልም ነው ያሉት።

እንዲሁም የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲው በአምስት ክፍለ ከተሞች አውደ ርዕይ እና ባዛር ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በ800 ሱቆች፣ 205 የህዝብ ተቋማት እና 200 ልኳንዳ ቤቶች አማካኝነት ነው አገልግሎት እየሰጠ ያለው።

ለሸማቹ ማህበረሰብ ከሚሰጠው አገልግሎት ባለፈም አሁን ላይ ከ1 ሺህ በላይ ለሚደርሱ አቅመ ደካሞች እና ህጻናት በቋሚነት ድጋፍ ያደርጋል።

በሲሳይ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.