Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ የብሄራዊ ስታዲየም ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስራው ከ4 ዓመት በፊት የተጀመረው በኢትዮጵያ ግዙፍ የተባለውና በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው ብሄራዊ ስታዲየም የመጀመሪያው ምእራፍ የግንባታ ተጠናቆ፤ ሁለተኛ ምእራፍ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምር ተገለፀ።
 
በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እየተገነባ ያለው ስታዲየም 62 ሺህ ስዎችን የመያዝ አቅም አለው።
 
ከስታዲየሙ ሜዳ ሳር ማልበስና የመሮጫ ትራክ በስተቀር በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያው ምእራፍ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ የህንፃውን መዋቅር ጨምሮ የስፖርተኞች ማረፊያ፣ ቢሮዎች፣ የጋዜጠኞች ማስተናገጃን ያካትታል።
 
የመጀመሪያው ምእራፍ የፕሮጀክቱ ሥራ በተወሰነ ጊዜ የዘገየ ሲሆን ለዚህም ምክንያቶቹ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች በጊዜው አለመድረስና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተጠቅሰዋል።
 
በቅርቡ ይጀምራል ተብሎ በሚጠበቀው ሁለተኛው ምእራፍ የስታዲየሙ ፕሮጀክት ከሚካተቱት ሥራዎች መካከል የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም ይገኙበታል።
 
ከዚህም ሌላ ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ የሄሊፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራና ሌሎች በርካታ ስራዎች ይከናወናሉ ተብሏል።
 
ሁለተኛውን ምእራፍ ሥራ ለማጠናቀቅ በጠቅላላው 900 ያህል ቀናት እንደሚፈለግ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል።
 
የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር እንዳሉት፥ ለመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከ2 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።
 
ሁለተኛው ምእራፍ የግንባታ ሥራ ከዚህ የበለጠ ወጪ ይጠይቃል ብለዋል።
 
ለሁለተኛው ምእራፍ ሥራ የኮንትራክተር ጨረታ ወጥቶ አሸናፊው የተለየ ሲሆን በቅርቡ የኮንትራት ውሉ እንደተጠናቀቀ ሥራው ይጀመራል ሲሉም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
 
ስታዲየሙ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን ከማስተናገድ በተጨማሪ ሌሎች እንደ አትሌቲክስ አይነት ውድድሮችን ለማስተናገድ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው።
 
ምንጭ፦ ኢዜአ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.