Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራርና አባላት የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተመንግስት ንቅናቄ ላይ ተሳተፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራርና አባላት የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተመንግስት ንቅናቄ ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን እውነታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ላይ መሳተፋቸው ተገለፀ፡፡
አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ በመነሳት እና ህፃናትን ጭምር በማሰለፍ በከፈተው ጦርነት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ከማድረሱም በላይ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡
ይሁን እንጂ አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እና አንዳንድ የውጪ መገናኛ ብዙሃን የአሸባሪውን ድርጊት ከማውገዝ ይልቅ በተሳሳተ እና እውነታውን ባላገናዘበ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሷል፡፡
በነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት ሃገር አቀፍ ንቅናቄ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ካቢኔያቸው የህወሓት የሽብር ቡድንን ዓላማ እና እንቅስቃሴ በግልፅ ተረድተው የሽብር ቡድኑን ተጠያቂ እንዲያደርጉ፣ በተሳሳተ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ የሚነዛው አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ እና በኢትዮጵያ ላይ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመመከት የሚያስችሉ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፥ የተቋሙ አመራርና አባላትም በንቅናቄው ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን እውነታ ለማሳወቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ መደገፋቸውን አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ፣ ምክትል ኮሚሽነሮች ፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና አባላት ወደ ነጩ ቤተመንግስት የሚላከውን መልዕክት በመሙላት እና በነጭ ፖስታ በማሸግ እንደ ፀጥታ አስከባሪ ሃይል ብቻ ሳይሆን እንደዜጋም የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ጭምር ያደረጉት ተሳትፎ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.