Fana: At a Speed of Life!

የአገሪቷን ኪነ-ሕንፃ ታሪክና አካባቢን ያገናዘበ ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች በሚከወኑ ልማቶች ታሪክ፣ ባሕልና ማንነትን ያገናዘበ ኪነ-ሕንፃ እንዲኖር ለማድረግ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።

የጋራ መግባቢያ ሰነዱን በቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ዳይሬክተር ሙሳ ከድር እና የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋማርያም ተሾመ ተፈራርመዋል።

የቱስሪት መዳረሻ ልማትን የተመለከተ የጋራ ውይይት ትናንት በአዳማ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር፣ የቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የባህልና ቱሪዝምና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተወካዮች በተሳተፉበት ውይይት ኪነ-ሕንፃ ለቱሪዝም ያለውን አስተዋጽኦ የተመለከቱ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል።

በዚህም በከተሞች እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች ቀደምት ታሪክና የአካባቢ ሁኔታን ያላገናዘቡ መሆናቸው እንዲሁም ቅርሶች ለልማት ተብለው መፍረሳቸው የአገር ማንነት ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ተገልጿል።

የቱሪስት መዳረሻ ልማት ዳይሬክተሩ ሙሳ ከድር ከማኅበሩ ጋር የተደረገው ስምምነት በቱሪዝም ኢትዮጵያ የልማት ስራዎች ውስጥ የኪነ-ሕንፃ ባህል በምን መልኩ እንደሚንፀባረቅ በትብብር መስራት ያስችላል ብለዋል።

ቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማትና የማስተዋወቅ ተልዕኮውን ሲወጣ ማኅበሩ እንዲያግዘውም ያደርጋል።

በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የቱሪስት ማዕከልና ሌሎች ልማቶች ሲሰሩ የአገሪቷን ኪነ-ሕንፃ ባህል እንዲያንፀባርቅ ከማኅበሩ የሙያ ምክርም ያስገኛል።

ሆቴሎች ሲገነቡ፣ ፓርኮች ላይ የተለያዩ የቱሪዝም ልማት ስራዎች ሲሰሩ ማኅበሩ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ የሚያስችል እንደሆነም አቶ ሙሳ ተናግረዋል።

የመግባቢያ ሰነዱን ስምምነቶች መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሃግብር እንደሚዘጋጅና ከቱሪዝም ጋር ተያያዥ ተግባራት ከሚያከናውኑ፣ መዳረሻዎችን ከሚያስተዳድሩና ቅርሶችን ከሚንከባከቡ ተቋማትም ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋማርያም ተሾመ ማኅበሩ በአገር ደረጃ ህንፃዎች፣ ከተሞች፣ የሕዝብ መናኸሪያ ቦታዎች ኀብረተሰቡን በሚጠቅም መልኩና በጥራት እንዲሰሩ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በአገሪቷ ‘የሚገነቡ ሕንፃዎችና በሕንፃዎች የሚገነቡ ከተሞች ማንነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል’ ያሉት አቶ ተስፋማርያም የሚስተዋሉት ግን የማይናበቡ ስራዎች ናቸው ብለዋል።

ሕንፃ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር አካባቢያዊ ጉዳዮችን በኪነ-ሕንፃ ማንፀባረቅና የቀደሙ ታሪኮችና ባህላዊ አሰራሮችን ፈጠራ በማከል ማንነትን የሚገልፅ ግንባታ ማከናወን እንደሚቻል ገልፀዋል።

ከተሞች የታሪክና የስልጣኔ መገለጫ በመሆናቸው ሕንፃዎችን አካባቢያዊ ጥናት በማድረግ የማኅበረሰቡን ማንነትና ባህል እንዲገልፁ ማድረግ እንደሚቻል ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በስምምነቱ መሰረት ቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪዝምን ምርት ምንነትና ቱሪስቶች ምን እንደሚሹ ያውቃል፤ አርክቴክቱ ደግሞ በኪነ-ሕንፃ እውቀቱ እገዛ እንዲያደርግ ያስችላል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.