Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ሕዝብ ዛሬም ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ዋጋ እየከፈለ ነው – የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአፋር ሕዝብ ዛሬም እንደ ጥንቱ ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ለሀገሩ ሉዓላዊነት ዋጋ እየከፈለ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አሰያ ከማል አስታወቁ።
አፈ ጉባዔዋ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በሰመራ ከተማ ሲከበር እንደተናገሩት÷ የክልሉ ሕዝብ ለሰንደቅ ዓላማውና
ለሀገሩ ባለው ፍቅር ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የአሸባሪውን ህወሓት ጥቃት ለማክሸፍ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው።
የክልሉ ሕዝብ አሸባሪው ቡድን የሀገሪቱን ዋነኛ የገቢና ወጪ ንግድ መሥመር ለመዝጋት የነበረውን ዕቅድ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፎ በመፋለም ድባቅ በመምታት ማክሸፉን ገልጸዋል።
ሕዝቡ ለሀገሩ ሉአላዊነትና ለሰንደቅ ዓላማው ክብርም ማናቸውንም ዋጋ ለመክፈል እንደቀድሞ ሁሉ ዛሬም ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኑን አፈ ጉባኤዋ አረጋግጠዋል።
እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአፋር ህዝብ የማንነት መገለጫው የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በማስከበር ለሀገሩ ሉዓላዊነት ታሪካዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፋር የሃይማኖት መሪ የነበሩት ሱልጣን ዓሊ ሚራህ በአንድ ወቅት “ሰንደቅ ዓላማችንንና የሀገራችንን ዳርድንበር እንኳን እኛ ግመሎቻችንንም ጠንቅቀው ያውቃሉ” ያሉትን ታሪካዊ ንግግር የጠቀሱት ወይዘሮ አሰያ÷ የአሁኑም ትውልድ በተግባር ለኢትዮጵያና ለሰንደቅ ዓላማው ያለውን ፍቅር አረጋግጧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.