Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ገቢ በዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የቢሮው ኃላፊ አቶ መሀመድ ሀሰን ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፥ ገቢው ቀጥተኛ፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ የግብር ታክሶችና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የተገኘ ሲሆን÷ አፈጻጸሙም የእቅዱን 82 በመቶ ነው።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የዘንድሮው በ304 ሚሊዮን ብር እድገት እንዳለው ገልጸዋል።

የህወሃት የሽብር ቡድኑ በክልሉ የፈጸመው ወረራ እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ገቢን በቅንነት አሳውቆ በወቅቱ የመክፈል ልምድ አለመጎልበት ለእቅዱ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት ሃላፊው በምክንያትነት ከጠቀሷቸው ጉዳዮች ዋነኞቹ መሆናቸውን የኢዜአ ዘገባ ጠቁሟል።

በገቢ አሰባሰቡ ሂደት የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በተካሄደው እንቅስቃሴ ባለፉት ወራት ዘጠኝ ወራት ግብርን ያለአግባብ ለመሰወር በሞከሩ 26 ድርጅቶች ላይ የገንዘብ ቅጣትና የማስጠንቀቂያ እርምጃ መወሰዱንም ኃላፊው ገልጸዋል።

በቀሪ ወራት የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ለገቢ አሰባሰቡ ትኩረት ሰጥቶ የንግድ ማህበረሰብ ግንዛቤና ደረሰኝ የመስጠት ልምዱ ለማዳበር የንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.