Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሀገራት በቅርብ ጊዜያት የኮቪድ19 መከላከያ ቁሳቁስ እጥረት ሊያጋጥማቸው ይችላል – አፍሪካ ሲዲሲ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ሀገራት በቅርብ ጊዜያት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል አስታወቀ።

ማዕከሉ ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ሀገራት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁስቁስ እጥረት ለመቅረፍ ሊዘጋጁ እንደሚገባ አሳስቧል።

የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው የአቅርቦች ሰንሰለት ችግር ምክንያት የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት ሊያጋጥማቸው ይችላል ብሏል ባወጣው መግለጫ።

41 ሀገራት የፊት ጭምብል መጠቀምን አስገዳጅ ማድረጋቸውን ያስታወሰው ማዕከሉ በተለይም የህክምና ባለሙያዎች የግለሰብ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት እንዳያጋጥማቸው ማድረግ ይገባል ነው ያለው።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቋቋሙ አካላትም በእቅዶቻቸው ውስጥ የመከላከያ ቁሳቀሶች እጥረት እንዳያጋጥም የሚያስችሉ ተግባራትን ሊያከናውኑ እንደሚገባ መግለፁን ሺንዋ ዘግቧል።

ቀድሞም ቢሆን በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት እንደነበር ሲነገር ቆይቷል።

በመሆኑም ከነበረው ችግር ጋር ተዳምሮ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በምታደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር በብዙዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.