Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ህብረት ለኮቪድ 19 የሚውል 300 ሚሊየን ዶላር ሊያሰባስብ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ህብረት ኮቪድ19ን ለመከላከል የሚረዳ 300 ሚሊየን ዶላር ሊያሰባስብ መሆኑን አስታወቀ፡፡
 
ህብረቱ ገንዘቡን የሚያሰባሰበው ጥቅምት 14 በዌቢናር በሚያካሂደው ዝግጅት ላይ ነው ተብሏል፡፡
 
የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ በህብረቱ ይፋዊ የስራ ቋንቋዎች አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ፖርቹጊዝ ይተላለፋል ነው የተባለው፡፡
 
በዝግጅቱ ገንዘብ ከማሰባሰብ በተጨማሪ በኮቪድ 19 ዙሪያ የግንዝቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደሚኖርም ነው የተሰማው፡፡
 
ህብረቱ ከዚህ ቀደም 44 ሚሊየን ዶላር ያሰባሰበ ሲሆን የአሁኑ 300 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
 
የሚሰበሰበው ገንዘብ ኮቪድ 19 በአህጉሪቱ እያደረሰ ያለውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመከላከል፣ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከልን አቅም ለማጎልበትና ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል የሚውሉ የህክምና ቁሳቁሶች ግዢ እና ስርጭት ይውላል ነው የተባለው፡፡
 
በዌብናሩ ዝግጅት ላይ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ፣ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
 
ለሁለት ሰዓታት በሚቆየው በዚህ የዌቢናር ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያዊቷ ቤቲጂን ጨምሮ በአህጉሪቷ የሚገኙ አርቲስቶች፣ የህብረቱ አመራሮች፣ ባንኮች እና የተለያዩ የንግድ ተቋማት እንደሚሳተፉ ከህብረቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
በአብርሃም ፈቀደ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.