Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የ830 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተስማማ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎች የሚውል የ830 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ፈርሟል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ከግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በጋና አክራ ሲያካሂድ የነበረው ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል።

የባንኩ የኃይል፣ የኢነርጂ፣ የአየር ንብረትና የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ኬቨን ካሪዩኪ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች የሚውል የ830 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት የገንዘብ ድጋፉ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም አስመልክቶ ከተዘጋጀው የኢንቨስትመንት ፈንድ የሚሰጥና ባንኩ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት እንደሚመራው ተገልጿል።

ገንዘቡ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ የዝዋይ-ሻላ ንዑስ ተፋሰስ የአየር ንብረት ለውጥ ተኮር የውሃ ሃብት ልማትና የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ስራዎች ላይ እንደሚውል የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ አስታውቋል።

በድጋፉ ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክት የውሃ ደኅንነትና አስተዳደር አቅምን የማጠናከር እንዲሁም በሐይቆች ላይ ያለውን ብዝሃ ሕይወት የመጨመር ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

በፕሮጀክቱም በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ የግብርና ሥራ የሚያከናውኑ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል።

በዓመታዊ ስብሰባው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ኢትዮጵያን ወክለው ተሳትፈዋል።

ባንኩ በአሁኑ ሰአት ግምታቸው 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የሚሆኑ በትራንስፖርት፣ ኢነርጂ፣ ውሃ፣ ግብርናና የግሉ ዘርፍ ልማት ዘርፎች እየተከናወኑ ለሚገኙ 23 ፕሮጀክቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ኢዜአ በዘገባው አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.